Fana: At a Speed of Life!

የባንግላዴሽ ባለሃብቶችን የኢንቨስትመንት ተሳትፎ ለማሳደግ እየተሰራ እንደሆነ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የባንግላዴሽ ባለሃብቶችን በኢትዮጵያ ያላቸውን የኢንቨስትመንት ተሳትፎ ለማሳደግ እየተሰራ እንደሆነ ተገለጸ።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሰሃ ይታገሱ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ የባንግላዴሽ አምባሳደር ሲክደር ቦዱሩዝማን ጋር ተወያይተዋል።

የውይይታቸው ዓላማ በልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች የባንግላዴሽን ባለሀብቶችን ተሳትፎ ለማሳደግና ባንግላዴሽን በአልባሳትና በመድሃኒት ቅመማ ዘርፍ ያላትን እምቅ እውቀትና ሀብት ከኢንቨስትመንት ጋር በማስተሳሰር በኢትዮጵያ ጥቅም ላይ ሊውል የሚችልበትን አውድ ለማመቻቸት መሆኑ ተገልጿል።

ፍሰሃ ይታገሱ (ዶ/ር) በሀገር አቀፍ ደረጃ የተተገበረው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች ያለውን የባንግላዴሽ ባለሀብቶች ተሳትፎ የሚያሳድግ መሆኑን ገልፀው፤ አመርቂ ያልሆነውን የባንግላዴሽ ባለሃብቶች ተሳትፎ ለማሳደግ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በተለይም በአልባሳት ዘርፍ የባንግላዴሽን ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ያላቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ ከኤምባሲዉ ጋር በትብብር መስራት እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

እንደሀገር ለውጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር የሚያስችሉ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች እየተተገበሩ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

ለዘርፉ የሚያስፈልጉ መሰረተ ልማቶች የተሟላላቸዉ የኢኮኖሚ ዞኖች፣ ወጣትና የሰለጠነ የሰዉ ሃይል፣ ጥራቱን የጠበቀ የግብዓት አቅርቦት መኖራቸው እንዲሁም ለዓለም አቀፍ ገበያ ያለዉ መልክዓ-ምድራዊ አቀማመጥና ሌሎች ምቹ ሁኔታዎች ኢትዮጵያን ተመራጭ ያደርጋታል ብለዋል።

አምባሳደር ሲክደር ቦዱሩዝማን በበኩላቸው፥ ኤምባሲዉ ከኮርፖሬሽኑ ጋር ተቀራርቦ ለመስራት ፍላጎት እንዳለው አንስተዋል፡፡

ኢትዮጵያም በዘርፉ ከፍተኛ የማምረትና የገበያ አቅም ያላት ሀገር መሆኗን አንስተው፥ መልክዓ-ምድራዊ አቀማመጧ ባለሀብቶችን ወደዓለም ገበያ ለመድረስ የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የባንግላዴሽ ባለሃብቶችን በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ የሚኖራቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ ስራዎች መጀመራቸዉን ጠቅሰዋል፡፡

በዚህም ከጨርቃጨርቅና አልባሳት በተጨማሪ በፋርማሲዩቲካል ዘርፍ ባለሀብቶችን ለማምጣት የሚያስችሉ መድረክ ለማዘጋጀት ስራዎች መጀመራቸዉን አብራርተዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.