በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ከመኸር እርሻ 2 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል ምርት ተሰበሰበ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከመኸር እርሻ እስካሁን 2 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል ምርት መሰብሰቡን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ምክትል ኃላፊ አሸናፊ ክንፉ በምርት ዘመኑ 7 ነጥብ 6 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን ጠቁመው እስካሁን በተደረገው ርብርብ 68 በመቶ ምርት ለመሰብሰብ እንደተቻለ ገልጸዋል።
ከ110 ሺሕ ሄክታር በላይ ማሳ ላይ ያለው ምርት አለመሰብሰቡን የገለጹት ምክትል ኃላፊው ይህም በክልሉ ባለው በተለያየ የአየር ጸባይ አንፃር በደጋ እና ወይናደጋ አካባቢዎች ምርቶቹ ለመሰብሰብ ባለመድረሳቸው እንደሆነ ለፋና ዲጂታል ሚዲያ አስታውቀዋል።
በክልሉ በ2016/17 ምርት ዘመን በመኸር እርሻ 345 ሺሕ 600 በላይ ሄክታር መሬት በሰብል መሸፈኑን ገልጸው ከዚህ ውስጥ 253 ሺሕ ሄክታር በላይ ለአጨዳ መድረሱን ተናግረዋል።
የምርት አሰባሰብ ሂደት ከጥቅምት መጨረሻ ጀምሮ እየተከናወነ መሆኑን አንስተው ይህም እንደየአካባቢው አየር ፀባይ እስከ ጥር አጋማሽ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
እስካሁን በተሰራው የምርት አሰባሰብ ሂደት ጤፍ፣ ስንዴ፣ ሩዝ፣ ቦሎቄና አተር የመሳሰሉ ምርቶች ከተሰበሰቡ ምርቶች መካከል እንደሚገኙም አመላክተዋል።
በየአካባቢው የደረሱ ምርቶችን ኅብረተሰቡ የተለያዩ አደረጃጀቶችን በመጠቀም እየሰበሰበ መሆኑን ያመላከቱት ኃላፊው የምርት ብክነት እንዳይኖር የግብርና ባለሙያዎች ክትትልና ድጋፍ እያደረጉላቸው እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
ኅብረተሰቡም የደረሱ ሰብሎች በጊዜና በተቀናጄ መንገድ በመሰብሰብ የምርት ብክነት እንዳይከሰት የበኩሉን ኃላፊነት እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
በአድማሱ አራጋው