የመሬት መንቀጥቀጥ የከፋ ጉዳት እንያዳስከትል ጥንቃቄ …
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ሰሞኑን በገቢ ረሱ ዞን የተለያዩ ቀበሌዎች የመሬት መንቀጥቀጥ በተደጋጋሚ እየተስተዋለ መሆኑ ይታወቃል፡፡
በአዋሽ 7 ከተማ አሥተዳደር፣ በአዋሽ ፈንታሌ እና አሚባራ ወረዳዎች በሚገኙ የተወሰኑ ቀበሌዎች የመሬት መንቀጥቀጥ በተደጋጋሚ እየተከሰተ መሆኑን የዞኑ ዋና አሥተዳዳሪ አብዱ ዓሊ ለፋና ዲጂታል ትናንት ማሳወቃቸው ይታወሳል፡፡
ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜም ከ30 በላይ መኖሪያ ቤቶች ጉዳት እንደደረሰባቸው እና በመንገዶች እንዲሁም ማሳዎች ላይ የመሰነጣጠቅ ሁኔታ እየተስተዋለ መሆኑን ተናግረው ነበር፡፡
ይህን መነሻ በማድረግም በቀጣይ የከፋ ጉዳት እንዳይከሰት ምን መደረግ አለበት? ስንል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂኦ ፊዚክስ ሕዋ ሣይንስ እና አስትሮኖሚ ተቋም የሴስሞሎጂ ትምህርት ክፍል ኃላፊ፣ የመሬት መንቀጥቀጥ ሣይንስ መምህርና ተመራማሪ የሆኑትን አታላይ አየለ (ፕ/ር) ጠይቀናል፡፡
በምላሻቸውም ሰሞኑን በተደጋጋሚ የመሬት መንቀጥቀጥ ጠንከር ብሎ እየተስተዋለ መሆኑን አንስተው÷ ለአብነትም ቅዳሜ ረፋድ 4 ሠዓት ከ43 ላይ በሬክተር ስኬል 5 የተመዘገበ የመሬት መንቀጥቀጥ ተከስቷል ብለዋል፡፡
በተጨማሪም እሁድ ማለዳ 12 ሠዓት ከ57 ላይ 4 ነጥነብ 9 እንዲሁም በዚሁ ዕለት ምሽት 2 ሠዓት ገደማ በሬክተር ስኬል 5 የሆነ የመሬት መንቀጥቀጥ መከሰቱን እና ሌሎችም ክስተቶች መኖራቸውን ጠቅሰዋል፡፡
አደጋው በዚህ ቀን ይከሰታል ወይም አይከሰትም ማለት ስለማይቻል÷ የአካባቢው አሥተዳደርም ሆነ ሕብረተሰቡ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ ይበጃቸዋል ብለዋል፡፡
ምናልባት ከዚህ በከፋ ሁኔታ የመሬት መንቀጥቀጥ ቢከሰት እና የአለት ወደ ውጭ መፍሰሰ ቢያጋጥም ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር የምትገናኝበት የባቡር እና የመኪና መንገድ መስተጓጎል እንዳያስከትል መጠንቀቅ እንደሚገባ መክረዋል፡፡
ተገቢው ጥንቃቄ ካልተደረገ እና ክስተቱ ካጋጠመ በኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ችግሮችን ሊያስከትል እንደሚችል አስገንዝበዋል፡፡
በአካባቢው በሚኖሩ ወገኖች እንዲሁም ተቋማት ላይም ጉዳት እንዳይደርስ መጠንቀቅ እንደሚገባ ነው የመከሩት፡፡
በዮሐንስ ደርበው