Fana: At a Speed of Life!

የቱርክ ኩባንያዎች ከማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች በመነሳት በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፣ ጥር 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የቱርክ ኩባንያዎችና ባለሃብቶች ከማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች በመነሳት በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ጥሪ አቀረቡ፡፡

አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በጽህፈት ቤታቸው በኢትዮጵያ የቱርክ አምባሳደር በርክ ባራን ጋር ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስሮችን ማሳደግ እንዲሁም በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ደህንነት ላይ ያለውን ትብብር ማጠናከርን ጨምሮ በሁለትዮሽ፣ ቀጣናዊና ባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።

አምባሳደር ምስጋኑ በኢትዮጵያና በቱርክ መካከል ያለውን ጠንካራ የሁለትዮሽ ግንኙነት አጽንኦት ሰጥተው ፥ በንግድና ኢንቨስትመንት ላይ ያላቸውን ግንኙነት የበለጠ ማሳደግ እንደሚገባ አስረድተዋል።

የቱርክ ኩባንያዎችና ባለሃብቶች በሀገሪቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተደረጉ ካሉት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች በመነሳት በኢንቨስትመንት ዘርፎች እንዲሳተፉም ጥሪ አቅርበዋል።

በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መካከል የተፈረመውን ስምምነት በተሳካ ሁኔታ እውን እንዲሆን ለተደረገው ጥረት የቱርክ ህዝብና መንግስትን አመስግነዋል።

አምባሳደር ባራን በበኩላቸው ፥ በአንካራ ስምምነት የኢትዮጵያና የሶማሊያ መንግስታት የገቡትን ቃል አድንቀዋል ነው የተባለው፡፡

በቆይታቸውም ዘርፈ ብዙ ግንኙነቶችን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ያላቸውን ቁርጠኝነት መግለጻቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.