Fana: At a Speed of Life!

ለረጂም ጊዜ የቆዩ 6 የመልካም አሥተዳደር ችግሮች ተፈትተዋል- ባለስልጣኑ

አዲስ አበባ፣ ጥር 10፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ብቁ አሽከርካሪና ብቃቱ የተረጋገጠ ተሽከርካሪ ለማፍራት ተግዳሮት ሆነው ለረጂም ጊዜ የቆዩ ሥድስት የመልካም አሥተዳድር ችግሮች መፈታታቸውን የአሽከርካሪና ተሽከርካሪ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

በባለስልጣኑ የአሽከርካሪ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ በድሉ ሌሊሳ፥ ብቁ አሽከርካሪና ብቃቱ የተረጋገጠ ተሽከርካሪ ለማፍራት ተግዳሮት ሆነው ለረጂም ጊዜ ቆዩ ሥድስት የመልካም አሥተዳድር ችግሮች ባለፉት ሥድስት ወራት መፈታታቸውን አስታውቀዋል፡፡

ለአብነትም የደረጃ መንጃ ፈቃድ እድሳት ዕድሜቸው ከ55 በላይ ለሆናና አዲስ ጊዜያዊ መንጃ ፈቃድ ከያዙ ውጭ በ4 ዓመት እንዲታደሱ መደረጉ አንዱ መሆኑን ጠቅሰው÷ በዚህም የ408 ሺህ አሽከርካሪዎች ጥያቄ ተፈትቷል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም የዕጩ አሽከርካሪዎች የተግባር መለማመጃ ቦታ እጥረት መቀረፉ፣ የአጭር የጽሑፍ መልዕክት መጀመሩ፣ ከኮድ 3 ወደ ኮድ 2 የአገልግሎት ለውጥ ካደረጉ የስም ዝውውር ለማድረግ አንድ ዓመት ይጠብቁ የነበሩ ወደ ሶስት ወር ዝቅ መደረጉ እና ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች በጨረታ ሲሸጡ ወቅታዊ የዋጋ ግምት ማስተካከያ መደረጉን ዘርዝረዋል፡፡

ለረጂም ጊዜ የቆዩት የመልካም አሥተዳደር ችግሮች በቴክኖሎጂ የተደገፈ ቀልጣፋና ውጤታማ አገልግሎት በመስጠትና የሕዝቡን እንግልት ለመቀነስ በተወሰደው አቋም የተፈቱ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

እንዲሁም ወደ ውጭ ለሚጓዙ ተገልጋዮች የኢንተርናሽናል መንጃ ፈቃድ ማረጋገጫ ለማግኝት በመንጃ ፈቃዳቸው ብቻ አገልግሎት እንዲሰጣቸው መደረጉን አረጋግጠዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.