Fana: At a Speed of Life!

አቶ አደም ፋራህ “ጋዲሳ ኦዳ” የአንድ ማዕከል አገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓትን ጎበኙ

አዲስ አበባ፣ ጥር 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ በአዳማ ከተማ የሚገኘውን “ጋዲሳ ኦዳ” የአንድ ማዕከል አገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓትን ጎበኙ፡፡

ማዕከሉ በሁሉም የከተማ አስተዳደሩ ተቋማት የሚሰጡ አገልግሎቶችን በተናበበና በተቀናጀ መልኩ በአንድ ማዕከል ለመስጠት የተቋቋመ መሆኑን አቶ አደም በማኅበራዊ ትሥሥር ገጻቸው ገልጸዋል፡፡

29 ዘርፎችን በአንድ ማዕከል በማሰባሰብ በቴክኖሎጂ በተደገፈ አግባብ ቀልጣፋና ውጤታማ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

ይህ ሥርዓት የባለጉዳዮችን እንግልት የቀነሰ፣ ገቢን ለመሰብሰብ ምቹ የሆነ፣ ልማዳዊ የሆነውን የወረቀት ሥርዓት ከ80 በመቶ በላይ በሁሉም ዘርፎች ውስጥ ያስቀረ እንዲሁም የአሰራር ግልፅነትና ተጠያቂነትን ለማስፈን ብሎም ሌብነትንና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል ከፍተኛ እድል የፈጠረ ነው ሲሉም አብራርተዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ በከተማ ደረጃ ያሉ ተቋማትን በአንድ ማዕከል ከማሰበሰብ ባሻገር የክፍለ-ከተማ እና የወረዳ ተቋማትም በአንድ ማዕከል እንዲሰሩ ማድረጉ እጅግ የሚበረታታና ለሌሎች ከተማ አስተዳደሮችም ተሞክሮ የሚሆን ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም በከተማ አስተዳደሩ በኩል ባለፉት ዓመታት በተሰሩ ስራዎች መሬትን ሙሉ ለሙሉ በካዳስተር ቴክኖሎጂ ዲጂታል ለማድረግ የተሄደበት ርቀት፣ በከተማዋ የሚኖሩ ዜጎች ደህንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን ለማስቻል የተዘረጋው የሲሲቲቪ ካሜራ ዝርጋታ ውጤታማነት በሁሉም የሀገራችን ክፍሎች በምርጥ ተሞክሮነት ተወስዶ ተግባራዊ እንዲደረግ እንደ ብልፅግና ፓርቲ ልዩ ትኩረት ሰጥተን በቀጣይ የምንሰራበት ይሆናል ብለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.