Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ በየዓመቱ 80 ሺህ ሰዎች በካንሰር ይያዛሉ

አዲስ አበባ፣ ጥር 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ)የአፋር ክልል ጤና ቢሮ በዱብቲ አጠቃላይ ሆስፒታል የካንሰር ህክምና ማዕከል አገልግሎት አስጀመረ።

 

በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ የጤና ሚኒስቴር ተወካዮች፣ የክልሉ ጤና ቢሮ አመራር አካላት፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

 

በጤና ሚኒስቴር የካንሰር መርሐ ግብር አስተባባሪ ታከለች ሞገስ በዚሁ ወቅት እንዳሉት÷ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በየዓመቱ 80 ሺህ ሰዎች በካንሰር ይያዛሉ።

 

ከሚያዙት ውስጥም 67 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸውን ገልጸው÷ በተለይም በማህፀንና በጡት ካንሰር የሚያዙ ሴቶች ቁጥር በርካታ መሆኑን አመልክተዋል።

 

ይሁንና የጡትና የማህፀን ካንሰር በጊዜ ህክምና ከተደረገ መዳን የሚችል በመሆኑ ማዕከሉ ለዚህ አገልግሎት ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ነው ያስረዱት።

 

የአፋር ክልል ጤና ቢሮ ሃላፊ ያሲን ሃቢብ÷ የማዕከሉ ስራ መጀመር ረጅም ርቀት በመጓዝ የሚታከሙ ሰዎች ህክምናውን በአቅራቢያቸው እንዲያገኙ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

 

በተለይም አርብቶ አደር እናቶች የሚበዙበት አካባቢ መጀመሩ ከግንዛቤ ማሳደግ ጀምሮ በርካታ ፋይዳዎች እንደሚሰጣቸው መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.