Fana: At a Speed of Life!

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዓላማ እንዲሳካ የሁሉም ዜጋ ተሳትፎ አስፈላጊ ነው – ተስፋዬ ቤልጅጌ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ጥር 13፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የተቋቋመለት ዓላማ እንዲሳካ የሁሉም ዜጋ ተሳትፎ አስፈላጊ መሆኑን የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ ቤልጂጌ (ዶ/ር) ገለጹ።

ተስፋዬ ቤልጅጌ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ እንዲሁም የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታን ለማጠናከር በተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት ዙሪያ በሰጡት ማብራሪያ፥ በኢትዮጵያ ለዘመናት እየተንከባለሉ የመጡ ስብራቶችን ለማከም ዘርፈ ብዙ ተግባራት መከናወናቸውን አንስተዋል።

በተለይም የፖለቲካና የምጣኔ ሃብት ስብራቶችን ለመጠገን መሰራቱን አንስተዋል።

በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በመነጋገር የጋራ መግባባት ለመፍጠር የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በተሳካ መልኩ ስራውን እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ የቆዩ ችግሮችን በንግግር በመፍታት ጠንካራ ሀገረ-መንግስትና ህብ-ብሔራዊ አንድነትን መፍጠር የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉም ነው ያሉት።

ብልጽግና ፓርቲ በምክክር ሀገራዊ ችግሮችን በዘላቂነት መፍታት ይቻላል የሚል ፅኑ አቋም በመያዝ የሚጠበቅበትን ሃላፊነት እየተወጣ ይገኛል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የተቋቋመለት ዓላማ ከዳር እንዲደርስ የሁሉም ዜጋ ተሳትፎና እገዛ አስፈላጊ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

ከችግርና ጉስቁልና ወጥታ የበለጸገችና ለዜጎቿ የምትመች ሀገር ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት መደገፍና ማገዝ ተገቢ መሆኑንም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ የፖለቲካ አካሄድ በአካታችና አሳታፊነት በሃሳብ የበላይነት እንዲመራ በማድረግ ረገድ የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑን ማረጋገጣቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.