የ20 ኢትዮጵያውያን ህይወት በጀልባ መስጠም አደጋ አለፈ
አዲስ አበባ፣ ጥር 14፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ቅዳሜ ምሽት ላይ 35 ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ከየመናዊ ካፒቴን እና ረዳት ካፒቴን ጋር የያዘች ጀልባ ከጂቡቲ ተነስታ በባኒ አል-ሃካም ከተማ አል-ሃጃጃህ አቅራቢያ መስጠሟን በየመን የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት አስታወቀ።
በአደጋው የዘጠኝ ሴቶች እና የ11 ወንዶች ህይወት በድምሩ የ20 ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ህይወት ማለፉ ተገልጿል።
ከአደጋው የቀሩት 15 ኢትዮጵያውያን እና ሁለት የየመን የበረራ ሰራተኞች መትረፋቸውን ማወቅ ተችሏል።
አክሎም ህገ-ወጥ ስደትን ለመከላከል በርካታ ጥረቶች ቢደረጉም በፈረንጆቹ 2024 ብቻ ከ60ሺህ በላይ መደበኛ ያልሆኑ ስደተኞች ወደ የመን መድረሳቸውን ድርጅቱ ገልጿል።
በጅቡቲ የኢትዮጵ ኤምባሲም ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በርካታ መደበኛ ያልሆኑ ስደተኞችን በየጊዜው ከጂቡቲ ወደ ሀገር ቤት የመመለስ ስራ እየሰራ ቢሆንም በህገ-ወጥ ስደት ምክንያት የበርካታ ዜጎቻችን አካል ከማጉደሉም በላይ የብዙዎችን ህይወት እየቀጠፈ ይገኛል ብሏል።
በመሆኑም ህብረተሰቡ እና የሚመለከተው መንግስታዊ አካል በሙሉ ይህን ህገ-ወጥ ተግባር ለመከላከልና የዜጎች ህይወት ለመታደግ በጋራ መስራት እንደሚያስፈልግ ኤምባሲው ጠይቋል።