Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ እና ፓኪስታን መካከል ፓርላሜንታዊ ግንኙነትን ለማጠናከር እንደሚራ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥር 14፣ 2017 (ኤፍ አኤም ሲ) በኢትዮጵያ እና ፓኪስታን መካከል ያለውን ፓርላሜንታዊ እና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር እንደሚሠራ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታወቀ፡፡

በምክር ቤቱ የውጭ ግንኙነት እና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዲማ ኖጎ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ የፓኪስታን አምባሳደር ከሆኑት አቲፍ ሻሪፍ ሚያን ጋር በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡

በዚሁ ወቅት ሁለቱ ሀገራት በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ እና በማህበራዊ ዘርፍ የቆየ ግንኙነት አላቸው ያሉት ሰብሳቢው÷ ይህንንም ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር እንደሚሰራ አረጋግጠዋል፡፡

በአፍሪካ ሰላም እና ደህንነትን ለማረጋገጥ ኢትዮጵያ እየተጫወተችው ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

በቀጣይም በተለያዩ የአፍሪካ ክፍሎች ጸረ-ሰላም ሀይሎችን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ከአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት ጋር በጋራ ትሰራለች ማለታቸውን የምክር ቤቱ መረጃ አመላክቷል፡፡

አምባሳደሩ በበኩላቸው የሀገራቱን ፓርላሜንታዊ ግንኙነት ለማጠናከር የሚያስችል የፓርላማ ወዳጅነት ቡድን አባላት የእርስ በእርስ የልምድ ልውውጥ የሚያደርጉበት መድረክ እንደሚፈጠር ጠቁመዋል፡፡

ሀገራቱ በተለያዩ የዓለም መድረኮች ላይ ብሄራዊ ጥቅሞቻቸውን እና ፍላጎቶቻቸውን ለማስጠበቅ በጋራ እንደሚሰሩም ገልጸዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.