የድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጣና ለሀገር የብልፅግና ጎዞ የድርሻውን እንዲወጣ በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ጥር 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጣና ለሀገር ሁለንተናዊ የብልፅግና ጉዞ የድርሻውን እንዲወጣ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሰሃ ይታገሱ (ዶ/ር) ተናገሩ።
በወጭና ገቢ ንግድ እንዲሁም በሎጂስቲክ ዘርፎች የሚሰማሩ ሰባት የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ባለሃብቶች በድሬደዋ ነፃ ንግድ ቀጣና ውስጥ የመስሪያ ቦታ ዛሬ ተረክበዋል።
ዋና ስራ አስፈፃሚው ፍሰሃ ይታገሱ (ዶ/ር) በዕለቱ እንደተናገሩት፥ ኢትዮጵያ በነፃ የንግድ ቀጣና ዘርፍ ተወዳዳሪና ተመራጭ መዳረሻ እንድትሆን በትጋት እየተሰራ ነው።
ነፃ የንግድ ቀጣናው ሁሉም መሰረተ ልማት ከተሟሉለት 58 ሄክታር መሬት ውስጥ 40 ሄክታሩ ለሀገር ውስጥና እና ለውጭ ባለሃብቶች መሰጠት መጀመሩን ተናግረዋል።
በዛሬው ዕለትም በወጭና ገቢ ንግድ፣ በሎጂስቲክስ እና በአገልግሎት ዘርፍ ለተሰማሩ ሰባት ባለሃብቶች የተሰጠው ቦታም የዚሁ ማሳያ መሆኑን ገልፀዋል።
ተመሣሣይ ጥያቄ ያቀረቡ ቀሪ 13 ባለሃብቶች በቅርብ ምላሽ እንደሚያገኙም ዋና ስራ አስፈፃሚው አክለዋል።
ዛሬ የተከናወነው የመስሪያ ቦታ ርክክብ በቀጣናው ውስጥ ከማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በተጨማሪም በአገልግሎት፣ በሎጂስቲክስ እና በንግድ ዘርፍ እንቅስቃሴዎች ለመጀመራቸው ማረጋገጫን የሚሰጥ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በእነዚህ ዘርፎች የሚደረገው እንቅስቃሴ ነፃ የንግድ ቀጣናውን ከፍታና ተወዳዳሪነት በማሳደግ በጅቡቲ ወደብ ላይ የሚደርሱ መጓተቶችና የምንዛሬ ወጪዎችን ማስቀረት እንደሚያስችልም ተናግረዋል።