Fana: At a Speed of Life!

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በግማሽ ቢሊየን ብር የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክቶች እየተተገበሩ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥር 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በ2017 ዓ.ም በግማሽ ቢሊየን ብር ወጪ የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክቶች እየተተገበሩ መሆኑን የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

አብርሃም በላይ (ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው÷ የአርብቶ አደሮች እና ከፊል አርብቶ አደሮችን ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክቶች በስኬት እየተጠናቀቁ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

በአሶሳ ከተማ ላይ ተግባራዊ የሆነው የአርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደሮች የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት ስራ አካል የሆነውን በቴክኖሎጂ የተደገፈ የእንስሳት እና የግብርና ምርታማነት ለማሻሻል ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው የፈሳሽ ናይትሮጅን ማምረቻ ፕሮጀክት ሎጅስቲክስ ስርዓቱ አሟልተን በማጠናቀቅ አስመርቀናል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ለህዝባችን ቅርብ ነን ስንል በምክንያት ነው ያሉት ሚኒስትሩ÷ በክልሉ በ2017 ዓ.ም በግማሽ ቢልየን ብር የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክቶች ተግባራዊ እየተደረጉ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡

በተመሳሳይ መልኩ በሌሎች የሀገራችን የአርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎችም በስፋት ተግባራዊ እያደረግን እንገኛለን ብለዋል፡፡

ፕሮጀክቶቹ በዓለም አቀፍ አጋር ድርጅቶች ድጋፍ ለዜጎች የኑሮ ማሻሻል ትርጉም ያለው ለውጥ የሚያመጡ መሆናቸውንም ተጠቃሚ ዜጎች በሄድንበት ሁሉ በደስታ ገልፀውልናል ሲሉም አንስተዋል፡፡

ለቀጣይ ዓመታትም ተመሳሳይ የኑሮ ማሻሻያ የልማት ስራዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉ ይሆናል ነው ያሉት፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.