ሁሉም ዜጋ ኢትዮጵያን ለዓለም በማስተዋወቅ ለሀገሩ አምባሳደር እንዲሆን ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ፣ ጥር 21፣ 2017(ኤፍ ኤም ሲ) ሁሉም ዜጋ የኢትዮጵያን ዕድገትና ደማቅ እሴቶች ለዓለም በማስተዋወቅ ለሀገሩ አምባሳደር ሊሆን እንደሚገባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
በሚኒስቴሩ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ዳይሬክተር ጀኔራል አምባሳደር ሽብሩ ማሞ ኢትዮጵያ ከጥንትም ለአፍሪካውያንና ለጥቁር ህዝቦች የነጻነት ቀንዲልና ተምሳሌት መሆኗን ጠቅሰው፥ ይህም በዓለም የዲፕሎማሲ ታሪክ ስሟን ገናና ያደረገ መሆኑን አውስተዋል።
ኢትዮጵያ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የህብረት ተቋማት እንዲመሰረቱ ታሪካዊ አሻራ እንዳላትም ጠቅሰዋል።
ከለውጡ ወዲህ የውጭ ግንኙነት ሥራዎች ላይ እመርታ መመዝገቡን ጠቁመው ፥ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ተምሳሌት የሆኑ የኢኮኖሚ ልማትና የዲፕሎማሲ ስራዎችን እያከናወነች ነው ብለዋል።
ከለውጡ ማግስት ባስመዘገብናቸው ስኬቶች በዓለም መድረክ ተደማጭነታችን እያደገ ነው ሲሉም ተናግረዋል አምባሳደሩ።
ኢትዮጵያ አዳዲስ ዓለም አቀፋዊ ስብስቦችን እየተቀላቀለች መሆኑን ጠቅሰው ፥ እንደ ብሪክስ ያሉ ጥምረቶች አባል መሆኗ በሁለትዮሽና በባለብዙ ወገን የትብብር መስኮች ተጠቃሚ እያደረጋት መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ጠንካራ ኢኮኖሚ እየገነባች መሆኗ ለቀጣናው ሰላም ጭምር ከፍተኛ ሚና ያለው ወታደራዊ አቅም መፍጠሯ ለዲፕሎማሲ ሥራዎቿ ትልቅ አስተዋፅኦ እያበረከተ ነው ብለዋል።
ከለውጡ ወዲህ በበርካታ የልማት ኢኒሼቲቮች በርካታ ለውጦች መመዝገባቸውን ገልጸው፥ በዚህም ኢትዮጵያ በርካታ ዓለም አቀፋዊ እውቅና እንዳገኘች ማንሳታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።