Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ የጥራት ደረጃውን የጠበቀ የኢኮኖሚ ለውጥ አይቻለሁ – አምባሳደር ሰልማ መሊካ

አዲስ አበባ፣ ጥር 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ የጥራት ደረጃውን የጠበቀ የኢኮኖሚ ለውጥ እንቅስቃሴን አይቻለሁ ሲሉ በኢትዮጵያ የአልጄሪያ አምባሳደር ሰልማ መሊካ ሀዳዲ ገለጹ።

አምባሳደሯ ከፋና ዲጂታል ጋር በነበራቸው ቀይታ÷በመሠረተ ልማት ረገድ በኢትዮጵያ ርዕሰ መዲና አዲስ አበባ ላይ ትልቅና አዎንታዊ ለውጥ መኖሩን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሩም በተቋማት ሪፎርም፣ በባንኮች፣ በቱሪዝም፣ ኤክስፖርት እና በሌሎች ዘርፎች ላይ ትልቅ ለውጥ ማየታቸውን ጠቅሰዋል።

ይህም ኢትዮጵያን በአህጉሪቱ በኢኮኖሚ አንደኛ ደረጃ ላይ ከሚገኙት ሀገራት ተርታ እንድትሰለፍ አድርጓታል ነው ያሉት፡፡

ኢትዮጵያ በትክክለኛ መስመር ላይ እንደምትገኝና ንቁ ሕዝብ እና አስተዋይ አመራር እንዳላት እንዲሁም የአህጉሪቱን የልማት አጀንዳዎች ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የበኩሏን አስተዋጽኦ እንደምታደርግ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ የብሪክስ ቡድንን በአባልነት መቀላቀሏ የመንግስት ጥረት ውጤት ማስረጃ መሆኑንም አንስተዋል።

የኢትዮጵያና የአልጄሪያ ግንኙነት ታሪካዊ መሆኑን ያነሱት አምባሳደሯ÷ ሁለቱ ሀገራት በፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር ሲሰሩ መቆየታቸውን አውስተዋል፡፡

በፈረንጆቹ 2022 የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአልጄሪያ ጉብኝት ከፕሬዚዳንት አብዱልማድጂድ ተቡኒ ጋር ያደረጉት ምክክር በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር ወሳኝ ሚና እንደነበረው ጠቅሰዋል።

የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት በማጠናከር ረገድ አልጄሪያ በተያዘው ዓመት በምታካሂደው 3ኛው የስታርትአፕ ጉባዔ ላይ ኢትዮጵያን በክብር እንግድነት ተሳታፊ ማድረጓን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያና አልጄሪያ በአፍሪካ ህብረት የተተካው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መስራቾች ውስጥ ግንባር ቀደም ሀገራት መሆናቸውንና አሁንም ሕብረቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ውጤታማ እንዲሆን የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ አስገንዝበዋል፡፡

በአሚር በድሩ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.