የኢትዮጵያና ሩሲያን ትስስር ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኑን የሩሲያው ዩናይትድ ፓርቲ አስታወቀ
አዲስ አበባ፣ ጥር 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያና ሩሲያን ትስስር ለማጠናከር የሩሲያው ዩናይትድ ፓርቲ ቁርጠኛ መሆኑን የብሪክስ አባል ሀገር እህት ፓርቲ የሩሲያው ዩናይትድ ላዕላይ ምክር ቤት ቢሮ አባል፣ የሩሲያ ፌዴሬሽን ሴናተር እና የሴኔቱ የውጭ ጉዳዮች ምክትል ኃላፊ አንድሬይ ክሊሞቭ ገለጹ፡፡
አንድሬይ ክሊሞቭ በአዲስ አበባ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በመዲናዋ የተለያዩ የቱሪስት መዳረሻዎችን እና የልማት ስራዎችን መጎብኘታቸውን ገልጸው፥ ከተማዋ በአስደናቂ ለውጥ ላይ መሆኗን አንስተዋል፡፡
ከተማዋ በመሰረተ ልማት፣ በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት እና በመዳረሻ ስፍራዎች ልማት ረገድ ዓለም አቀፍ ደረጃን የጠበቀ ሳቢነት ተላብሳለች ብለዋል።
ኢትዮጵያ በሁሉም መስኮች በፈጣን ለውጥ ላይ እንደምትገኝ ማረጋገጥ ችያለሁ ሲሉም በመግለጫቸው ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያና ሩሲያ ለ126 ዓመታት የዘለቀ ወዳጅነት እንዳላቸው አውስተው፥ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን በፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ እያጠናከሩ ስለመምጣታቸው ነው ያነሱት፡፡
ብልጽግና ፓርቲም የኢትዮጵያን ልማት፣ ሰላም እና ብልፅግና ለማረጋገጥ ትክክለኛ ቁመና ላይ ይገኛል ነው ያሉት፡፡
የብልጽግና ፓርቲ ፕሬዚዳንት ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለተሻለ ልማት፣ የሀገራት ትብብር፣ ልማትና እድገት ተቀባይነት ያለው ጥሪ አቅርበዋል ሲሉም ገልጸዋል ሴናተሩ፡፡
የሀገሪቱን እምቅ ሃብቶች እና ወጣት የሰው ኃይል አስተሳስረው የፓርቲውን ሀገራዊ እቅድ እንደሚያሳኩም ተስፋ አደርጋለሁ ብለዋል፡፡
የሁለቱን ሀገራት ፓርቲ ለፓርቲ፣ መንግስት ለመንግስት እና ሕዝብ ለሕዝብ ትስስር ለማጠናከርም ፓርቲያቸው ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
በወንደሰን አረጋኸኝ