Fana: At a Speed of Life!

የሕዝቡን የልማት ፍላጎት መሰረት በማድረግ በተተገበሩ ኢንሼቲቮች አበረታች ውጤት ተገኝቷል – አቶ ሽመልስ አብዲሳ

አዲስ አበባ፣ ጥር 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ባለፉት ዓመታት የሕዝቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ፍላጎት መሰረት በማድረግ በተተገበሩ ኢንሼቲቮች አበረታች ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ገለፁ።

የክልሉ መንግሥት ያለፉት ስድስት ወራት የመንግስትና የፓርቲ የሥራ ዕቅድ ክንውንን የሚገመግም መድረክ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡

ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ በዚህ ወቅት እንዳሉት፥ ባለፉት ዓመታት በመንግስትና በፓርቲው የተቀመጡ አቅጣጫዎችን ለመተግበር በተከናወኑ ሥራዎች ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል።

በተለይ በክልሉ ልማት፣ ሰላምና ዴሞክራሲን ለማጠናከር ከተከናወኑ ተግባራት በተጨማሪ ትምህርትና ቴክኖሎጂን በማስፋፋት በኩል ውጤታማ ስራ መሰራቱን ነው የተናገሩት።

የክልሉን ህዝብ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ፍላጎቶች ለማሳካት ተቀርጸው የተተገበሩ የተለያዩ ኢንሼቲቮች የተሻለና አበረታች ውጤት እየተመዘገበባቸው መሆኑን አስረድተዋል።

ኢንሼቲቮችን ወደ መሬት በማውረድ ከመተግበር አንፃር የተሻለ ክንውን ቢኖርም የህዝቡን የልማት ፍላጎት ሙሉ ለሙሉ ከመመለስ አንፃር አሁንም ከፍተት መኖሩን አመልክተዋል፡፡

የክልሉ መንግስት የህዝቡን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ አሁንም በሙሉ አቅሙ እየሰራ ይገኛል ነው ያሉት።

መድረኩ የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ የተከናወኑትን ከመገምገም ባለፈ ለቀጣይም የሥራ አቅጣጫ የሚቀመጥበት መሆኑን ተናግረዋል።

ግምገማው በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ጠቁመው÷በክልሉ ዘላቂ ሰላምን ትርጉም ባለው መልኩ ማረጋገጥና ለችግሮች ዘላቂ መፍትሔ መስጠት አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም ጠንካራ አደረጃጀት እስከ ቀበሌ መዘርጋትና አሰራርን እውን ማድረግ ትኩረት የሚሰጠው መሆኑን ጠቁመዋል።

ህብረተሰቡ አገልግሎትን በገንዘብ እየገዛ ነው ያሉት አቶ ሽመልስ÷ ሌብነትና ብልሹ አሰራርን ማስወገድ በየደረጃው ያለው አመራር ሃላፊነት እንደሆነ ማሳሰባቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.