በኦሮሚያ ክልል የ3 ሺህ 225 ቅድመ መደበኛ ት/ቤቶች ግንባታ ተጠናቀቀ
አዲስ አበባ፣ ጥር 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል አዳዲስ ትምህርት ቤቶችን የመገንባት እና የነባር ት/ቤቶችን ደረጃ የማሻሻል ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ፡፡
በቢሮው የእቅድና በጀት ዝግጅት ዳይሬክተር ሃሰን እንድሪስ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ባለፉት ስድስት ወራት በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት ተሰርቷል፡፡
በዚህ መሰረትም አዳዲስ ት/ቤቶችን የመገንባት፣ የነባር ት/ቤቶችን ደረጃ የማሻሻል እና የትምህርት ግብዓት ሥርጭት ሥራ መከናወኑን አንስተዋል፡፡
በግማሽ ዓመቱ በሕዝብ ተሳትፎ እንዲሁም በባለሃብቶችና አጋር አካላት ድጋፍ 5 ሺህ ቅድመ መደበኛ ት/ቤቶችን ለመገባንት ታቅዶ 3 ሺህ 225 ት/ቤቶች መገንባታቸውን ነው የገለጹት፡፡
በተጨማሪም 651 አንደኛ ደረጃ አዳዲስ ት/ቤቶች መገንባታቸውን የገለጹት ዳይሬክተሩ÷የ3 ሺህ 53 ነባር ትምህርት ቤቶች ደረጃ መሻሻሉንም ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም በተለያዩ አካባቢዎች ተማሪዎችን ከዲጂታል ቴክኖሎጂ ጋር የሚያስተዋውቁ ከ200 በላይ የቴክኖሎጂ ማዕከላት መገንባታቸውን ጠቁመዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ