አርሜኒያ ሥራዎችን በዲጂታል ሥርዓት ለማዘመን የሚደረገውን ጥረት እንደምትደግፍ ገለጸች
አዲስ አበባ፣ የካቲት 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) አርሜኒያ በሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የተጀመሩ ሥራዎችን በዲጂታል ሥርዓት ለማዘመን ለሚደረገው ጥረት ድጋፍ እንደምታደርግም አስታወቀች።
የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ የአርሜንያ አምባሳደር ሳክ ሳርጊሲያን ጋር ተወያይተዋል።
በውይይታቸውም ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) የኢትዮ-አርሜንያ ወዳጅነት ዘመናትን የተሻገረ መሆኑን አውስተዋል፡፡
ሁለቱ ሀገራት ሰፊ የታሪክ፣ የሃይማኖት እና የባህላዊ ትውፊት ባለቤት እንዲሁም በማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ መስኮች ጠንካራ ግንኙነት ያላቸው መሆኑን አንስተዋል።
በስርዓተ ፆታ እኩልነት፣ በማኅበራዊ ጥበቃ፣ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት፣ጥቃትን በመከላከል ረገድ ያሉ በጎ ተሞክሮዎችን መለዋወጥ በሚያስችሉ ነጥቦች ላይ በጋራ ለመስራት ከስምምነት ላይ መደረሱንም የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል።
አምባሳደር ሳክ ሳርጊሲያን በበኩላቸው÷ሀገራቸው በተለይ በኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ ያላትን ሰፊ ልምድና እውቀት ለማካካፈል እንደምትፈልግ ገልጸዋል።