38ኛውን የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ ከ1 ሺህ በላይ ጋዜጠኞች ሽፋን ይሰጣሉ
38ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤን ከ1 ሺህ በላይ ጋዜጠኞች ሽፋን ይሰጣሉ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) 38ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤን ከአንድ ሺህ በላይ ጋዜጠኞች ሽፋን ይሰጡታል ተብሎ እንደሚጠበቅ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን አስታውቋል፡፡
38ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ከየካቲት 8 እስከ 9/2017 ዓ.ም የሕብረቱ መቀመጫ በሆነችው አዲስ አበባ ከተማ ይካሄዳል፡፡
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የአፍሪካ ሕብረት ብሄራዊ የጉባዔ አመቻች ኮሚቴ አባል በመሆን ጉባዔው በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅና የሚዲያ ሽፋን እንዲያገኝ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡
ከእነዚህም መካከል ስብሰባውን ለሚዘግቡ የሀገር ውስጥና የውጭ ጋዜጠኞች “ፕሬስ ፓስ” እንዲያገኙ ማድረግ፤ ወደ ኢትዮጵያ ለሚመጡ የውጭ መገናኛ ብዙኃን አካላት የመዳረሻ ቪዛ የማመቻቸት እና ለሙያ መገልገያ መሳሪያዎቻቸው የከስተም ክሊራንስ ስራዎችን መስራት ዋና ዋናዎቹ መሆናቸው ተገልጿል።
እነዚህን ስራዎች ቀልጣፋ ለማድረግ በቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ጉምሩክ፤ በአፍሪካ ሕብረት ባጅ ሴንተር እንዲሁም በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና መስሪያ ቤት በቂ የሰው ኃይል በመመደብ የተቀላጠፈ የ24 ስዓት አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኝም ባለስልጣኑ ገልጿል።
የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔን ለመዘገብ እስካሁን 390 የሀገር ውስጥ እና 530 የውጭ ጋዜጠኞች መመዝገባቸውን ባለስልጣኑ ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን በላከው መረጃ አስታውቋል።
በዚህ ሂደት ሚዲያዎች ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ በማስቻልና የእንግዳ ተቀባይነታችንን በማረጋገጥ ስብሰባው መልካም ገፅታን አጉልቶ በማሳየት ይጠናቀቅ ዘንድ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ባለስልጣኑ ጥሪ አቅርቧል፡፡