ኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ የብልጽግና ፓርቲ የትኩረት አቅጣጫ ነው – ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ የካቲት 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነትን እውን በማድረግ የኢትዮጵያን ብልጽግና ማረጋገጥ የብልጽግና ፓርቲ ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን የፓርቲው ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የገንዘብ ሚኒስትር ዴዔታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ገለጹ።
በ2ኛው የብልጽግና ፓርቲ መደበኛ ጉባዔ ባለፉት ሦስት ዓመታት ፓርቲው ለሕዝብ የገባውን ቃል በብዙ ጥረትና የተቀናጀ ሥራ እያሳካ እንደቆየ ተገምግሟል።
ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)÷ብልጽግና ከዚህ በፊት የጀመረውን ዘርፈ ብዙ የልማትና የእድገት ሥራዎች በማጠናከር የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ስብራት ለመጠገን አዳዲስ ሀገር በቀል ሃሳብ ይዞ የመጣ ፓርቲ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ፖርቲው በዜጎች መካከል መለያየትን ይፈጥር የነበረውን የፖለቲካ እሳቤ ከመሰረቱ የቀየረ ነው ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡
በኢኮኖሚው መስክ ሰፋፊ የሪፎርም ሥራዎች ሲከናወኑ እንደቆዩ ማንሳታቸውን ከፓርቲው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የመጀመሪያው የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ተጠናቆ በሁለተኛው የኢኮኖሚ ሪፎርም በዋና ዋና ዘርፎች ጠንካራ ተወዳዳሪ የኢኮኖሚ ማዕቀፍ በመገንባት በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በቱሪዝም፣ በማዕድን እና በዲጂታል ኢኮኖሚ ልማት መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር በማምጣት የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልፅግና ማረጋገጥ መቻሉን አብራርተዋል፡፡
በ2023 ኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልጽግና የተረጋገጠባት አፍሪካዊት የብልጽግና ተምሳሌት እንድትሆን የሚያግዝ ስራ በቁርጠኝነት፣ በትጋትና በታማኝነት መስራት እንደሚገባም አሳስበዋል።