Fana: At a Speed of Life!

ከክልሉ የቡና ሽፋን ውስጥ 66 ሺህ ሄክታሩ የምርት መቀነስ ይታይበታል ተባለ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ካለው የቡና ሽፋን ውስጥ 66 ሺህ ሄክታር የሚሸፍነው ያረጀና ምርት መቀነስ የሚታይበት መሆኑን የክልሉ የቡና፣ ሻይና ቅመማቅመም ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

የባለስልጣኑ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይ ኮጁአብ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት ክልሉ 582 ሺህ 139 ሄክታር የቡና ሽፋን ያለው ሲሆን÷በዚህም 513 ሺህ ያህል አርሶ አደሮች በቀጥታ በዘርፉ ተሰማርተዋል፡፡

237 በቡና ኢንቨስትመንት ዘርፍ የተሰማሩ ባለሃብቶች መኖራቸውን ጠቁመው÷በዚህም 59 ሺህ 263 ሄክታር መሬት በቡና ተሸፍኗል ብለዋል፡፡

በክልሉ ካለው 582 ሺህ 139 ሄክታር የቡና ሽፋን ውስጥ 350 ሺህ 69 ያህሉ ምርት የሚሰጥ ሲሆን÷ ቀሪው ደግሞ ገና ለምርት ያልደረሰ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ከቡና ምርታማነት ማሻሻያ ሥራዎች አንፃር በክልሉ ምርት ከሚሰጠው ቡና ሽፋን ውስጥ 66 ሺህ ሄክታር የሚሸፍነው ያረጀና ምርት መቀነስ የሚታይበት በመሆኑ በጉንዳላና በነቀላ የማደስ ሥራ በስፋት እየተሰራ ይገኛል ነው ያሉት፡፡

ከዚህ አንፃር ባለፋት 3 ተከታታይ ዓመታት 10 ሺህ 158 ሄክታር በአማካይ በዓመት 3 ሺህ 500 ሄክታር ማሳ መታደሱን አብራርተዋል፡፡

በ2017 በጀት ዓመትም 4 ሺህ 820 ሄክታር ማሳ ለማደስ መታቀዱን ገልፀው÷አስካሁን 2 ሺህ 440 ሄክታር ወይም 50 በመቶ ያህሉን ማደስ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

በፌቨን ቢሻው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.