ከኢራን የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ጋር ለመሥራት ያለመ ስምምነት ተፈረመ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ከኢራን የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩትና የውጭ ጉዳይ አካዳሚ ጋር በትብብር መሥራት የሚያስችለውን ስምምነት ፈረመ፡፡
የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ጃፋር በድሩ በኢትዮጵያ ከኢራን አምባሳደር ዓሊ አክባር ራዚ ጋር ተወያይተዋል፡፡
በዚሁ ወቅትም የኢትዮጵያ እና የኢራን ፖሊሲ አውጪዎች፣ ምሁራን እና ባለሙያዎች የሚሳተፉበት የጋራ ኮንፈረንስ ለማዘጋጀት ከስምምነት መደረሱን የኢንስቲትዩቱ መረጃ አመላክቷል፡፡
ኮንፈረንሶቹ የሀገራቱን ሰላምና ደኅንነት ለመጠበቅ፣ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ለማምጣት እና የባሕል ዲፕሎማሲን ለማዳበር ብሎም ዓለም አቀፍ እና ቀጣናዊ ተግዳሮቶችን ለመፍታት አስተዋፅኦ ይኖራቸዋል ተብሏል፡፡
የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት እና የኢራን የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩትና የውጭ ጉዳይ አካዳሚ የሀገራቱ የጋራ ጉዳዮች በሆኑ ቀጣናዊ ጂኦፖለቲካ፣ ንግድ ብሎም የኢትዮጵያ እና ኢራንን ትስስር የሚያጠናክሩ ጥናቶችን ለማድረግ ተስማምተዋል፡፡