በኦሮሚያ ክልል ከ212 ሺህ በላይ ተማሪዎች ሀገር አቀፍ ፈተና ይወስዳሉ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል በዘንድሮ የትምህርት ዘመን ከ212 ሺህ በላይ ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ሀገር አቀፍ ፈተና እንደሚወስዱ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ገለጸ።
የቢሮው ኃላፊ ቶላ በሪሶ (ዶ/ር) ለፋና ዲጂታል እንደገለጹት፤ በክልሉ የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና በወረቀት እና ኦን ላይን ይሰጣል።
በክልሉ ከ212 ሺህ በላይ ተማሪዎች ሀገር አቀፍ ፈተና የሚወስዱ ሲሆን 59 በመቶ የሚሆኑት የተፈጥሮ ሳይንስ፤ 41 በመቶ ደግሞ የማህበራዊ ሳይንስ ተፈታኝ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ከተፈታኝ ተማሪዎች መካከል 47 በመቶ የሚሆኑት ሴት ተማሪዎች እንደሆኑ ጠቁመዋል።
ከ50 ሺህ በላይ የሚሆኑ ተማሪዎች ፈተናውን በኦንላይን የሚወስዱበት ሁኔታ እየተመቻቸ መሆኑን ጠቅሰው፤ ተማሪዎች ፈተናውን በኦንላይን የሚወስዱባቸው ማዕከላት እየተለዩ ሁኔታዎችን የማመቻቸት ሥራ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ለፈተናው የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ለማሟላት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ስለመሆኑም የቢሮ ኃላፊው አመልክተዋል።
በፀሐይ ጉሉማ