Fana: At a Speed of Life!

ከ13 ሺህ 500 ጊጋ ዋት ሰዓት በላይ ኃይል ማመንጨት መቻሉ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ አጋማሽ 13 ሺህ 504 ነጥብ 2 ጊጋ ዋት ሰዓት ኃይል ማመንጨት መቻሉን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።

በተቋሙ የኃይል ማመንጫዎች ኦፕሬሽን ዘርፍ የዕቅድ ቢሮ ሥራ አስኪያጅ ጥሩወርቅ ሽፈራው፤ በኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ላይ በራስ አቅም የተከናወኑ የጥገና ሥራዎች የኃይል ምርት አፈፃፀምን ለማሳደግ ማስቻላቸውን ገልጸዋል።

በተከዜ እና በጢስ አባይ 2 ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች በብልሽት ምክንያት የቆሙ ተርባይኖችን እንዲሁም በግልገል ጊቤ 2 ኃይል ማመንጫ ጣቢያ የኖዝል ጫፍ ጥገና በማከናወን የጣቢያዎቹን የኃይል ምርት ማሻሻል እንደተቻለ ጠቁመዋል።

የኦፕሬሽንና የጥገና ሥራዎች ላይ ተጽዕኖ በማያሳድር እና የግድቦችን ደህንነት ለመጠበቅ እንዲያስችል የሞሉ ግድቦችን ውሃ የማስተንፈስ እንዲሁም የኃይል ማመንጨት ሂደቱን የሚያስተጓጉሉ ተንሳፋፊ ሳሮችን የመከላከል ተግባራት መከናወናቸውንም ገልጸዋል፡፡

በጣቢያዎቹ በራስ ኃይል የተከናወኑ የጥገና ሥራዎች የኃይል ምርት አፈጻጸሙን በማሳደጋቸው በስድስት ወራት 13 ሺህ 504 ነጥብ 2 ጊጋ ዋት ሰዓት ኃይል እንዲመነጭ አስችሏል ማለታቸውን የተቋሙ መረጃ አመላክቷል።

ይህም የዕቅዱን 15 ነጥብ 6 በመቶ ብልጫ ያለው መሆኑን ነው ስራ አስኪያጇ ያመላከቱት፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.