Fana: At a Speed of Life!

በኃይል መሰረተ ልማቶች ላይ የሚፈጸም ስርቆት እየቀነሰ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎች ላይ የሚፈጸሙ የስርቆት ወንጀሎችን ለመከላከል በተሰራው ሥራ ውጤት እየተገኘ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታውቋል፡፡

በተቋሙ የኃይል መሰረተ ልማት ደህንነት፣ ክትትልና ቁጥጥር ቢሮ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዋለ ታምሬ እንዳሉት÷በብረት ምሰሶዎች ላይ የሚፈጸምን ስርቆት ለመከላከል በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አቅጣጫ ተሰጥቷል፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎትም ለሚመለከታቸው አካላት በኃይል መሰረተ ልማቶች ላይ እየተፈፀመ ያለው ስርቆት የሀገሪቱ ብሔራዊ የደህንነት አጀንዳ እንደሆነ የማስገንዘብ ሥራ መስራቱን ተናግረዋል።

ተደጋጋሚ የስርቆት ወንጀል የሚፈፀምባቸው 21 መስመሮች መለየታቸውን ጠቁመው÷ተቋሙ ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ጋር ጠንካራ የመረጃ ልውውጥ ሥርዓት መዘርጋቱን ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል በግማሽ ዓመቱ በተለያዩ አካባቢዎች በኃይል ማስተላለፊያ መሰረተ ልማቶች ስርቆት ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ መከናወኑን አንስተዋል፡፡

በዚህም ማሕበረሰብ በመሰረተ ልማቶቹ ላይ ያለው የእኔነት ስሜት እያደገ እንደመጣ መናገራቸውን የተቋሙ መረጃ ያመላክታል፡፡

በግማሽ ዓመቱ በኃይል ማስተላለፊያ ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎች ላይ የተፈጸመው ስርቆት ካለፉት ዓመታት ተመሳሳይ ጊዜያት ጋር ሲነፃፀር እየቀነሰ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡

በቀጣይም የታየውን መሻሻል አጠናክሮ ለማስቀጠል ዜጎች የኃይል ማስተላለፊያ ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎችን እንዲጠብቁ የሚያግዙ ሥርዓቶች መዘርጋታቸውን አንስተዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.