በቤተ-ሙከራዎች ጊዜ ያለፈባቸው ኬሚካሎች ቆጠራ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ የካቲት 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ቤተ-ሙከራዎች ውስጥ የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው ኬሚካሎች ቆጠራ እየተካሄደ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
በሚኒስቴሩ የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ የምርምርና ማህበረሰብ ጉድኝት ተጠባባቂ መሪ ሥራ አስፈጻሚ ሰራዊት ሃንዲሶ (ዶ/ር) እንዳሉት÷ የምርምር ግብዓቶችንና ፋሲሊቲዎችን በማሻሻል የቤተ-ሙከራ ደረጃና አክሬዲቴሽን ሥርዓትን ለመዘርጋት እየተሰራ ነው፡፡
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚገኙ የኢንዱስትሪ፣ የምርምርና የላቦራቶሪ ኬሚካሎች አያያዝ፣ ክምችት፣ የማጓጓዝ ሒደትና የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸውን ኬሚካሎች ቆጠራ በትኩረት እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡
ለዚህም ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አካዳሚክ ቴክኒካል ረዳት ባለሞያዎች ስልጠና መሰጠቱን ነው የተናገሩት፡፡
በተጨማሪም በ2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች ስር ባሉ ቤተ-ሙከራዎች ውስጥ የሚገኙ ኬሚካሎችን ምንጭ፣ አይነት፣ ደረጃና መጠን የማወቅና መረጃ የማሰባሰብ ሥራ እንደሚሰራ መናገራቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል።