የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል እድል ፈጥረዋል
አዲስ አበባ፣ የካቲት 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ዕድል መፍጠር መቻሉን የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር) ገለፁ።
የመስኖ ልማት ስራ በተበታተነ መልኩ ሲሰራ መቆየቱን ያወሱት ሚኒስትሩ፤ በዝናብ ጥገኛ የሆነ የእርሻ ስራ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ባለመሆኑ የመስኖ መሰረተ ልማት ግንባታ በልዩ ትኩረት ራሱን ችሎ እንዲመራ ተደርጓል ብለዋል፡፡
በዚህም ሚኒስቴሩ ከዚህ ቀደም በተለያዩ ተቋማት ሲሰሩ የነበሩ የመስኖ ልማት ስራዎችና የቆላማ አካባቢ የኑሮ ማሻሻያ ተግባራትን አስተባብሮ እየመራ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ይህም ከፕሮጀክት ጥራትና መጓተት ጋር የሚነሱ ችግሮችን በማቃለል በፍጥነት ለማጠናቀቅ እንዳስቻለ ጠቅሰዋል።
በመስኖና ቆላማ አካባቢ እየተተገበሩ ባሉ ፕሮጀክቶች የተፈጠረው እድል የአካባቢውን ህብረተሰብ ምርትና ምርታማነት የሚያሳድግ ዕድል መፍጠሩንም ተናግረዋል።
ይህም ለሀገር ኢኮኖሚ አስተዋፅኦ የሚያበረክትና የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡