ወልድያን ለቱሪዝም ምቹ ለማድረግ የተከናወኑ ተግባራት የሚበረታቱ መሆናቸው ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የወልድያ ከተማን ለቱሪዝምና ኢንቨስትመንት ምቹ ለማድረግ የተከናወኑ ተግባራት የሚበረታቱ መሆናቸው ተገለጸ።
የአማራ ክልል ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ማማሩ አያሌውን (ዶ/ር) ጨምሮ ከፍተኛ የክልሉ የመንግስት ሥራ ኃላፊዎች በወልድያ ከተማ እየተሠሩ ያሉ የልማት ሥራዎችን ተመልክተዋል።
በጉብኝቱ ወቅት ማማሩ አያሌዉ (ዶ/ር)÷ የወልድያ ከተማ አስተዳደር የከተማዋን መሠረተ ልማት በማሟላት ለቱሪዝምና ኢንቨስትመንት ሳቢና ማራኪ፣ ለነዋሪዎቿም ምቹ ለማድረግ ያከናወናቸው ተግባራት የሚበረታቱ መሆናቸውን ገልፀዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዱባለ አብራሬ በበኩላቸው÷ ከተማው ውስጥ የተጀመሩ ፕሮጀክቶች በጥሩ አፈጻጸም ላይ እንደሚገኙ ገልፀው፤ ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው ጊዜ ለማጠናቀቅ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
የከተማዋ የኮሪደር ልማት እና የአስፓልት መንገድ ዝርጋታ ሥራዎችን እስከ መጋቢት 30 ለማጠናቀቅ እየተሠራ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡
ኅብረተሰቡ በሚሰሩ የተለያዩ ልማቶች ላይ የሚያሳየውን ተሳትፎና ተባባሪነት አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ማቅረባቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡