በሲዳማ ክልል በበጋ መስኖ 72 ሺህ ሄክታር ለማልማት ታቅዷል
አዲስ አበባ፣ የካቲት 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሲዳማ ክልል በዘንድሮው የበጋ መስኖ ከ72 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት መታቀዱን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡
የቢሮው ሃላፊ መምሩ ሞኬ÷በመስኖ ልማት የአርሶ አደሩን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና ገበያን ለማረጋጋት በተከናወኑ ሥራዎች ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን አመልክተዋል።
በመስኖ ልማት ገበያን ታሳቢ ያደረጉ አትክልቶችን የማምረት ሥራ ትኩረት እንደተሰጠው ገልጸው÷ልማቱም አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ ገበያን እያረጋጋ መሆኑን ገልጸዋል።
በክልሉ በመጀመሪያ ዙር ከ61 ሺህ ሄክታር የሚበልጥ መሬት በመስኖ ለምቶ የደረሰው ሰብል እየተሰበሰበ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በዘንድሮው የበጋ መስኖ ሥራም ከ72 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በማልማት ከ16 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ሃላፊው ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡