የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ ተጠያቂነት እንዲሰፍን ሚናውን በላቀ ደረጃ ሊወጣ ይገባል ተባላ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዲሰፍን ሚናውን በላቀ ደረጃ ሊወጣ ይገባል ሲሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ገለጹ።
“ዓላማ ተኮር፣ የተናበበ እና የተቀናጀ የተግባቦት ሥርዓት ለዕምርታዊ ዕድገት”በሚል መሪ ሃሳብ የጋራ የሚዲያ እና የኮሚኒኬሽን ጉባዔ እየተካሔደ ነው፡፡
ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት÷የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ በሀገር ሁለንተናዊ እድገት ውስጥ ጉልህ ሚና አለው፡፡
ስለሆነም ዘርፉ የህብረተሰብ ተሳትፎን ለማሳደግ እንዲሁም ሁሉን አቀፍ ለውጥ ለማምጣት ከመስራት በተጨማሪ ግልጽነት እና ተጠያቂነት እንዲሰፍን የተቀናጀ፣ የተናበበና የተደራጀ እንቅስቃሴ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
የተጀመሩ የልማት፣ የዴሞክራሲ ሥርዓት እና የሰላም ግንባታ ስራዎች እንዲጠናከሩ ዘርፉ የሚጠበቅበትን ሚና እንዲወጣ አሳስበዋል።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ከበደ ዴሲሳ በበኩላቸው÷ በግማሽ በጀት ዓመቱ ዘርፉ የመንግስት ዋና ዋና አጀንዳዎችን ከማስረጽ አኳያ ውጤታማ ስራዎች ማከናወኑን ገልጸዋል።
በተመሳሳይ ብሔራዊ መግባባትን ከመፍጠር አኳያ የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ ሁነቶችን በስፋት በመዘገብ አጀንዳ መፍጠር መቻሉን ተናግረዋል።
አሁንም አፍራሽ አጀንዳዎችን በመመከት የሰላም ግንባታውን እውን ለማድረግ የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ የበለጠ መስራት እንዳለበት አሳስበዋል።
በቀጣይም ዘርፉን የማጠናከር ስራ በትኩረት እንደሚከናወን የተገለፀ ሲሆን÷ በግምገማ መድረኩ ላይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ የፌዴራልና የክልል የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ ሃላፊዎች መሳተፋቸውን ኢዜአ ዘግቧል።