በአምራች ዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ በትኩረት እየተሰራ ነው – አቶ መላኩ አለበል
አዲስ አበባ፣ የካቲት 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ በትኩረትና በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ክሮታጅ ጣህኒ የሰሊጥ ማቀነባበሪያ ፋብሪካን በጎበኙበት ወቅት እንዳሉት÷በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች አስፈላጊው ድጋፍ እየተደረገ ነው፡፡
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውና የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ለዘርፉ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ወደ ውጪ ከሚላኩ የግብርና ውጤቶች መካከል ሰሊጥ ትልቅ ድርሻ እንዳለው ጠቁመው÷ፋብሪካው ሰሊጥ ምርት ላይ እሴት በመጨመር ለገበያ የማቅረቡን ሥራ እንዲያጠናክር አሳስበዋል፡፡
በዓመት እስከ 4 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ ሰሊጥ የማቀነባበር አቅም ያለው ፋብሪካው÷ እሴት የተጨመረበትን ሰሊጥ ወደ አሜሪካ፣ ሆላንድ፣ ፊላንድ እና እስራኤል እንደሚልክ ተጠቁሟል፡፡
ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ ማምረት ሲጀመር በዓመት 10 ሚሊየን ዶላር ገቢ ማስገኘት እንደሚችል የተገለጸ ሲሆን÷ በሙሉ አቅሙ ማምረት እንዲችልም የሚስተዋሉ ችግሮች እንዲፈቱ ተጠይቋል፡፡
በነፃነት ፀጋይ