በ2025 የኢትዮጵያ ኤክስፖ የሚሳተፉ አካላት ፕሮፖዛል እንዲያቀርቡ ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ በሚካሄደው የ2025 የኢትዮጵያ ኤክስፖ ላይ የሚሳተፉ ባለድርሻ አካላት ጥናታዊ ጽሑፍ እንዲያቀርቡ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አሥተዳደር እና የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ጥሪ አቀረቡ፡፡
ከፈረንጆቹ ግንቦት 16 እስከ 18 ቀን 2025 በአዲስ ኮንቬንሽን ማዕከል በሚካሄደው በዚህ ኤክስፖ ላይ፤ ተመራማሪዎች፣ ምሁራን እና የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ፕሮፖዛላቸውን እንዲያቀርቡ ተጋብዘዋል፡፡
ተሳታፊ ባለድርሻ አካላትም፤ በሰው ሠራሽ አስተውሎት እና ሳይበር ደኅንነት፣ በዘመናዊ ከተሞች እና ሳይበር ደኅንነት፣ በኳንተም ስሌት፣ በፋይን ቴክ እና በሰው ሠራሽ አስተውሎት ተዓማኒነት ዙሪያ ጥናታዊ ጽሑፍ እንዲያዘጋጁ ተጠይቋል፡፡
የጥናታዊ ጽሑፍ ማስገቢያ የመጨረሻ ቀን በፈረንጆቹ ሚያዝያ 20 እንዲሁም የውጤት ማሳወቂያ ጊዜ ሚያዝያ 30 ቀን 2025 መሆኑን ኢንስቲትዩቱ በማኅበራዊ ትሥሥር ገጹ አስታውቋል፡፡