Fana: At a Speed of Life!

የሩዝ ምርትን በሕገ ወጥ መንገድ ሽጠው ለግል ጥቅም አውለዋል ተብለው የተጠረጠሩ ግለሰቦች ተከሰሱ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ለማሕበረሰቡ በቅናሽ እንዲሸጥ የቀረበ የሩዝ ምርትን በሕገ ወጥ መንገድ ሽጠው ለግል ጥቅም በማዋል ሙስና ወንጀል የተጠረጠሩት ተከሰሱ።

የፍትሕ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ ትናንት ከሠዓት በኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን በቃሊቲ ፍጆታ ዕቃዎች ንግድ ሥራ ዘርፍ የመጋዘን ሥራ አስኪያጅ አድማሱ በቀለ ከበደ፣ በኮርፖሬሽኑ በቃሊቲ ፍጆታ ዕቃዎች ንግድ ሥራ ዘርፍ ረዳት የሽያጭ ሠራተኞች ጌትነት ኃይሉ ገ/ጻዲቅ እና ፍቃዱ በቀለ ጉርሜሳን ጨምሮ በሥድስት ተከሳሾች ላይ የተሳትፎ ደረጃቸውን ገልጾ የሙስና ወንጀል ክስ መስርቷል።

ይህም የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 ንዑስ ቁጥር 1(ሀ)፣ አንቀጽ 33 እና የሙስና ወንጀልን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀፅ 9 ንዑስ ቁጥር 1 (ሀ) ና ንዑስ ቁጥር 2 እንዲሁም በዚሁ በሙስና አዋጅ አንቀጽ 31 ንዑስ ቁጥር 1 እና 2 በተጨማሪነት ደግሞ በ1ኛ ተከሳሽ ላይ ብቻ አዋጅ ቁጥር 780/2005 አንቀጽ 29  ንዑስ ቁጥር 1 (ሀ) (ሐ) ሥር የተመለከተውን ድንጋጌ መተላለፍ የሚል ክስ በየደረጃው አቅርቧል።

በቀረበው ዝርዝር ክስ ላይ እንደተመላከተው፤ ተከሳሾች በጥቅም በመመሳጠር ለራሳቸው የማይገባ ጥቅም ለማግኘት በማሰብ መንግስት ገበያውን ለማረጋጋት በጃፓን መንግስት በኩል ከውጭ የገባ የሩዝ ምርትን በህብረት ሥራ ዩኒየኖች በኩል በዝቅተኛ ዋጋ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች እንዲሸጥና ለምግብ ዋስትና ፕሮጄክት ክፍያ እንዲውል አቅጣጫ የተሰጠበትን  4 ሺህ 668 ባለ 30 ኪሎ ግራም ከረጢት  ሩዝ ጥቅምት 2 ቀን 2016 ዓ.ም በ6 ሚሊየን 86 ሺህ 980 ብር ከ4ኛ እስከ 6ኛ ለተጠቀሱ ግለሰቦች በእጅ አዙር እንዲሸጥ ማድረጋቸው ተገልጿል፡፡

በዚህም ሩዙ ለታለመለት ዓላማ እንዳይውል በማድረግ ለራሳቸው ከ2 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር በላይ የማይገባቸውን ጥቅም ያገኙ መሆኑ የተሳትፎ ደረጃቸው ተጠቅሶ በክስ ዝርዝሩ ላይ ሰፍሯል።

በተጨማሪም  በ1ኛ ተከሳሽ በስሙ ከሩዙ ሽያጭ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተከፈተ ሂሳቡ ውስጥ ከገባው 2 ሚሊየን 700 ሺህ ብር  ውስጥ በተለያየ መጠን  ለተለያዩ ግለሰቦች ያስተላለፈ መሆኑ ተጠቅሶ፤ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ወንጀል ክስ ቀርቦበታል።

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 5ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎትም ትናንት በተከሳሾቹ ላይ የተመሰረተው የክስ ዝርዝር ለተከሳሾች እንዲደርስ በማድረግ ክሱን ለመመልከት ለመጋቢት 2  ቀን 2017 ዓ.ም ቀጥሯል፡፡

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.