የተሟላ ሀገራዊ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ሥራዎች የታሪክ እጥፋት የሚያመጡ ናቸው – አቶ አደም ፋራህ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ከተረጂነት በመላቀቅ የተሟላ ሀገራዊ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ሥራዎች የታሪክ እጥፋት የሚያመጡ መሆናቸውን የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ገለጹ።
ብልጽግና ፓርቲ ለሦስት ቀናት ሲያካሂድ የቆየውን የሥድስት ወራት የስራ አፈጻጸም ግምገማ አጠናቅቋል።
ጉባዔው በሦስተኛ ቀን ውሎው ከተረጂነት አስተሳሰብ ለማላቀቅና የቤተሰብ ምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ተግባራዊ የሆነውን መርሐ-ግብር አስመልክቶ በቀረበ የሱፐርቪዥን ሥራዎች ሪፖርት ላይ ተወያይቷል።
አቶ አደም በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ከተረጂነት ለመላቀቅ የተጀመረው ምርታማነትን የማሳደግ ተግባር ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።
በሀገር ደረጃ ተግባራዊ የተደረጉ እንደ ሌማት ትሩፋት፣ የከተማ ግብርና እና ሌሎች ኢኒሼቲቮች ማሳኪያ ግብ ሊሆኑ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
ከተረጂነት የመላቀቅ ሀገራዊ ንቅናቄ ሥራው ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ አመራሩ ለሥራው የሰጠው ልዩ ትኩረት የሚበረታታ መሆኑን ነው የገለጹት።
ከተረጂነት መላቀቅ የዓርበኝነት ምዕራፍ መሆኑን ያነሱት የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንት፤ የቀጣይ ሥራዎችን በፍጥነትና በመፍጠር መተግበር እንደሚገባ ተናግረዋል።
ከተረጂነት በመላቀቅ የተሟላ ሀገራዊ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ሥራዎች የታሪክ እጥፋት የሚያመጡ መሆናቸውንም አመላክተዋል።
በብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽሕፈት ቤት የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ የፖለቲካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ብሩክ ግዛው የሱፐርቪዥን ሪፖርቱን ባቀረቡበት ወቅት፤ ከተረጂነት ለመላቀቅ እየተከናወኑ የሚገኙ ሥራዎች ውጤት እያስገኙ መሆናቸውን ገልጸዋል።
መርሐ-ግብሩን ማሳካት የሚያስችል ዕቅድ መዘጋጀቱን፣ የመግባባት ሥራ በሁሉም ደረጃ መሠራቱን እንዲሁም ተጠቃሚዎች ከተረጂነት ለመውጣት ትክክለኛ አስተሳሰብ እንዲኖራቸው ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።
በተለይም ሊያጋጥሙ የሚችሉ አደጋዎችን በራስ አቅም ምላሽ ለመስጠት በየደረጃው እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች አበረታች መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በሴፍቲኔት መርሐ-ግብር ተጠቃሚ የሆኑ ዜጎች ዕድሉን በአግባቡ ተጠቅመው ከተረጂነት እንዲላቀቁ እየተደረገ ያለው ርብርብ አበረታች ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የንቅናቄ ሥራው በሁሉም አካባቢዎች ያለው የግንዛቤ፣ የአመለካከትና የዝግጁነት ወጥነትን ማስተካከል እንደሚገባም ተናግረዋል።
የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ከተረጂነት ወደ ምርታማነት የመሸጋገር ሂደት ከሐሳብ ወደ ተግባር መሸጋገር መጀመሩን ተናግረዋል።
ተረጂነትን ከመቅረፍ አኳያ ሰፊ ሥራ መሠራቱን ጠቁመው፤ ክልሎች የመጠባበቂያ እህል ክምችትን ለማሳደግ መሥራት እንዳለባቸው ገልጸዋል።
አመራር አባላት ግብዓቶችን ለአርሶ አደሮች ተደራሽ ከማድረግ አኳያ ሰፊ ሥራ መሥራት እንደሚጠበቅባቸውም አስገንዝበዋል፡፡
የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር)፤ ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመሸፈን የተጀመሩ ስራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።
የመጠባበቂያ እህል ክምችትን ማሳደግ ከሁሉም በላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ተግባራዊ መደረግ እንዳለበትም ጠቁመዋል።
የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ በበኩላቸው፤ በከተማ ሴፍቲኔት የታቀፉ ዜጎች ሰርተው ራሳቸውን እንዲችሉ የቁጠባ ባህላቸው እንዲያድግ ሥራዎች እየተከናወኑ ናቸው ብለዋል።
በዚህም በተጨባጭ ለውጥ በማምጣት ለሌሎች አርዓያ መሆን የሚችሉ ዜጎች ማውጣት መጀመሩን ጠቁመዋል።