የወንጀል ቅጣት አወሳሰን ረቂቅ መመሪያ ለተመሳሳይ ወንጀሎች ተቀራራቢ ውሳኔ ማሳለፍ ያስችላል ተባለ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በወንጀል ቅጣት አወሳሰን ላይ የተዘጋጀው ረቂቅ መመሪያ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለተመሳሳይ ወንጀሎች ተቀራራቢ ውሳኔ ማሳለፍ የሚያስችል መሆኑን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስታወቀ።
በተሻሻለው የወንጀል ቅጣት አወሳሰን ረቂቅ መመሪያ ላይ የቅጣት እርከን ያልነበራቸው የወንጀል አይነቶች መካተታቸውም ተገልጿል።
የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በወንጀል ቅጣት አወሳሰን ረቂቅ መመሪያ ላይ የክልልና ከተማ አስተዳደር የፍትሕ አካላት በተገኙበት በአዲስ አበባ የውይይት መድረክ አካሂዷል።
በዚሁ ጊዜ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ቴዎድሮስ ምህረት፤ የተሻሻለው የወንጀል ቅጣት አወሳሰን ረቂቅ መመሪያው የፍትሕ ሥርዓቱን ለማሻሻል በሚደረገው ጥረት ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል ብለዋል።
ረቂቅ መመሪያው በወንጀል ቅጣት ውሳኔ አሰጣጥ ሂደት የሚነሱ ቅሬታዎችን በመፍታት የወንጀል ሕጉን ግቦች ማሳካት በሚያስችል መልኩ ተገማች ውሳኔ ማስተላልፍ እንዲቻል መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
በተጨማሪም ረቂቅ መመሪያው የቅጣት ደረጃና እርከን ያልነበራቸው ወንጀሎችን በማካተት በፍርድ ቤት የሚሰጡ ውሳኔዎች ተቀራራቢና አስተማሪ እንዲሆኑ የሚያስችል መሆኑንም አስረድተዋል።
በተሻሻለው የወንጀል ቅጣት አወሳሰን ረቂቅ መመሪያው ላይ በአስገድዶ መድፈር፣ በሰው መግደልና ሌሎች የወንጀል ድርጊቶች የቅጣት እርከን ከፍ እንዲሉ መደረጉን አብራርተዋል።
በዚህም ዳኞች ለተመሳሳይ የወንጀል ድርጊቶች ተቀራራቢ፣ ተገማችና ተዓማኒ ውሳኔ ማሳለፍ ያስችላቸዋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡