Fana: At a Speed of Life!

 በሶማሌ ክልል የፖለቲካ ምኅዳሩን ለማስፋት በተሰጠው ትኩረት ከፍተኛ መሻሻል መምጣቱ ተገለጸ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሶማሌ ክልል የፖለቲካ ምኅዳሩን ለማስፋት በተሰጠው ትኩረት ከፍተኛ መሻሻል መምጣቱን የሶማሌ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ መሀመድ ሻሌ (ኢ/ር) ገለጹ።

በክልሉ አስተማማኝ ሰላም ከማስፈን ባሻገር የፖለቲካ ምኅዳሩን ለማስፋት በተሰጠው ከፍተኛ ትኩረት ዜጎች ሐሳብን በነፃነት መግለጽን ጨምሮ ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብታቸውን ከመቼውም ጊዜ በላይ በነፃነት እየተጠቀሙ መሆኑን ገልፀዋል።

ባለፉት የለውጥ ዓመታት በክልሉ ይከሰቱ የነበሩ የመብት ጥሰቶችን ለማስወገድ በተሠራው ጠንካራ ሥራ ለውጥ ማስመዝብ መቻሉን ጠቁመዋል።

ይህም የክልሉ ሕዝብ በነፃነት ሐሳቡን ከመግለፅ ባሻገር በልማት ሥራ ላይ እንዲያተኩር እንዳደረገው ተናግረዋል።

አክለውም፥ ለበርካታ ዓመታት ሕዝቡ ያላገኛቸውን እንደ ጤና፣ መንገድ፣ ትምህርት የመሳሰሉ የመሰረተ ልማት አውታሮች በስፋትና በጥራት መሠራታቸውን አንስተዋል፡፡

ይህንም ለማስቀጠልም በብልጽግና ፓርቲ የሚመራው መንግሥት በትኩረት እየሠራ ይገኛል ብለዋል።

ከለውጡ በኋላ ባሉት ዓመታት በክልሉ ያለው የፖለቲካ ምኅዳር አሳታፊና ምቹ እንዲሆን በመደረጉ ምክንያት የተለያዩ ፓርቲዎች ተመስርተው ወደ ፖለቲካው በመቀላቀል ከክልሉ አልፈው በሀገር አቀፍ ደረጃ በነፃነት እየተንቀሳቀሱ መሆኑ አንደኛው ትልቅ ስኬት መሆኑን ገልፀዋል።

ይሁንና የተገኘውን ስኬት ወደኋላ በሚጎትት መልኩ እዛና እዚህ ብቅ ብቅ የሚሉ አንዳንድ አካላትና ቡድኖች ሕዝብን በሚያራርቅ ሥራ ከመጠመድ ተቆጥበው ወደ ሕጋዊና እውነተኛ የፖለቲካ ሥራ መምጣት ይገባቸዋል ሲሉም አሳስበዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ወቅቱ የረመዳን ወር በመሆኑ የክልሉ መንግሥት ከሕዝቡ ጋር በመቀናጀት አቅመ ደካማ ዜጎችን የማብላትና የማልበስ ሥራ በስፋት እያከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል።

መሠረተ ቢስ ሐሰተኛ መረጃዎች በማሰራጨት የተጠመዱ አካላትና ቡድኖች ከእንዲህ አይነት የማይጠቅም ተግባር ተቆጥበው ሕዝብን በሚጠቅም መልካም ሥራ እንዲያተኩሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.