ቻይና የኢትዮጵያ የምንጊዜም የልማት አጋር ናት- አምባሳደር ተፈራ ደርበው
አዲስ አበባ፣ የካቲት 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ቻይና የኢትዮጵያ የምንጊዜም የልማት አጋር ናት ሲሉ በቤጂንግ የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈራ ደርበው ገለፁ፡፡
የኢትዮጵያ እና ቻይና ግንኙነት በጋራ ተጠቃሚነት እና እድገት መርህ ላይ የተመሰረተ መሆኑንም ነው አምባሳደሩ ያረጋገጡት፡፡
ሀገራቱ ባለፉት 55 ዓመታት በመሠረት ልማት ግንባታ፣በንግድ እና ኢንቨስትመንት እንዲሁም በኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ዘርፍ በትብብር ሲሠሩ መቆየታቸውን አውስተዋል፡፡
ባለፉት ዓመታት ቻይና በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስመንት ከፍተኛ ድርሻ ነበራት ያሉት አምባሳደሩ፤ አሁን ላይ ከ3 ሺህ በላይ የሀገሪቱ ኢንተርፕራይዞች በኢትዮጵያ ተሰማርተው እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
እነዚህ ኩባንያዎች ለመንግሥት ከሚያስገኙት ገቢ ባሻገር ለኢትዮጵያውያን ዜጎች በርካታ የሥራ ዕድሎችን መፍጠራቸውንም አብራርተዋል፡፡
ሁለቱ ሀገራት እንደ ቻይና አፍሪካ (ፎካክ) እና ብሪክስ በመሳሰሉ ቀጣናዊ እና አህጉራዊ የዲፕሎማሲ መድረኮች ላይ በትብብር እየሠሩ እንደሚገኙም አስገንዝበዋል፡፡
የኢትዮጵያ እና ቻይና የዲፕሎማሲ፣ የኢኮኖሚ፣ የሕዝብ ለሕዝብ እና ባህል ልውውጥ እየተጠናከረ መምጣቱንም አንስተዋል፡፡
በአጠቃላይ ቻይና ባለፉት 55 ዓመታት የኢትዮጵያ የምንጊዜም የልማት አጋር መሆኗን ነው ያነሱት፡፡
በቀጣይም ሁለቱ ሀገራት በኢንቨስትመንት፣ በቴክኖሎጂ ልኅቅት፣ በሰብዓዊ ግንባታ እና በፖለቲካ ዘርፍ ያላቸው ግንኙነት የበለጠ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያላቸውን እምነት ገልፀዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ