ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የስካይ ዊን ኤሮኖቲክስ ኢንዱስትሪን መረቁ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የስካይ ዊን ኤሮኖቲክስ ኢንዱስትሪን መረቁ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትሥሥር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ፤ ከጥቂት ዓመታት በፊት በሀገር ውስጥ ድሮን ስለማምረት ማሰብ የማይታሰብ ነበር ብለዋል፡፡
ብዙ አይነት ችሎታ ያላቸው ድሮኖችን በራሳችን ባለሙያዎች ዲዛይን አድርጎ የማምረት አቅም ትልቅ የታሪክ እጥፋት ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡
ይህን እድገት ለማዝለቅ ቀጣይነት ባለው የምርምር ሥራ ላይ፣ ገበያ በማስፋት ተግባር ላይ እና በሀገር ውስጥ የስማርት ሴንሰር ቴክኖሎጂዎችን በማምረት ላይ መሥራት ይገባናል ነው ያሉት፡፡
እንደዚህ እና እንደሆሚቾ የተተኳሽ ኢንጂነሪንግ ፋብሪካ ያሉትን አቅሞቻችንን የምናሳድገው፤ ግጭትን ለማቀጣጠል አይደለም፤ ግጭትን ለማስቀረት እንጂ ሲሉ በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡
ግጭትን በሚፈልጉ ተዋንያን ፊት ግጭትን ለማስቀረት የሚችል አቅም በመፍጠር ሰላም እና መረጋጋትን ለማፅናት ነው ፍላጎታችን ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።