Fana: At a Speed of Life!

ከተረጂነት ለመላቀቅ የተጀመሩ ሀገራዊ ጥረቶች እንዲሳኩ ርብርብ እየተደረገ ነው ተባለ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ከተረጂነት ለመላቀቅ የተጀመሩ ሀገራዊ ጥረቶችን ማሳካት የሚያስችል ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝ የብልጽግና ፓርቲ አመራሮች ገለጹ።

የብልጽግና ፓርቲ የ2017 በጀት ዓመት የሰባት ወራት የንቅናቄ ሥራዎች ግምገማ መድረክ አካሂዷል።

ከተረጂነት ለመላቀቅ የተከናወኑ ተግባራትና የተገኙ ውጤቶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

በዚሁ ጊዜም የብልጽግና ፓርቲ አመራሮች ከተረጂነት ለመላቀቅ እየተከናወኑ ባሉ ሥራዎችና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ አስተያታቸውን ሰጥተዋል።

በምክትል ርዕሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪና የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ በክልሉ ከተረጂነት መላቀቅ የሚያስችሉ ዕቅዶች ወጥተው ተግባራዊ እየተደረጉ ነው።

ምርት ላይ የሚሰሩ ስራዎችን ውጤታማነት ለማሳደግ እና የተሻለ አፈጻጸም ለማስመዝገብ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

እንዲያም ሆኖ አሁንም የበለጠ መስራት እንደሚገባ በግምገማ መለየቱን ገልጸው፤ በቀጣይ በትኩረት ይሰራል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በብልጽግና ፓርቲ የጋምቤላ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አሽኔ አስቲን በበኩላቸው፤ በክልሉ የግብርና ምርታማነትን የሚያሳደጉ አሰራሮች እየተዘረጉ መሆኑን ተናግረዋል።

ዘመናዊ የእርሻ መሳሪያዎችን ወደ ስራ ከማስገባት ባለፈ ምርጥ ዘርን ጨምሮ ምርታማነትን የሚያሳድጉ ግብዓቶችን ጥቅም ላይ የማዋል ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

በብልጽግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሞገስ ባልቻ፤ ሕብረተሰቡ እርስ በእርስ የሚረዳዳበት ስርዓት ተዘርግቶ ስኬታማ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን አንስተዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመንግስት ረዳት ተጠሪና በብልጽግና ፓርቲ የክልሉ የፖለቲካና የርዕዮተ-ዓለም ዘርፍ ኃላፊ አቶ ንጋቱ ዳንሳ እንዳሉት በክልሉ የመጠባበቂያ እህል ክምችትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው።

ለበልግ ወቅት ምርት የሚውል 6 ሺህ ሄክታር መሬት ተለይቶ ወደ ምርት ማስገባት የሚያስችል ዝግጅት ተደርጎ ወደ ስራ መገባቱንም አብራርተዋል።

የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መሥተዳድር አወሉ አብዲ በሰጡት አስተያየት፤ የተረጂነት አመለካከትን ለመቀየር በክልል ደረጃ የተከናወኑ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ውጤት እያመጡ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

በዚህም በክልሉ የተረጂነት አመለካከት ትርጉም ባለው ደረጃ መቀነሱን አንስተዋል።

የመጠባበቂያ እህል ክምችትን ማሳደግ ለሚያስችሉ መሰረተ ልማቶች ግንባታ እና ማስፋፊያ ስራዎች ትኩረት መሰጠቱንም አስረድተዋል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደርና የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ አንተነህ ፈቃዱ በበኩላቸው፤ ከተረጂነት ለመላቀቅ የተቀመጠውን አቅጣጫ ተከትሎ በክልሉ ተቋማዊ አደረጃጀት በመፍጠር ወደ ስራ መገባቱን ተናግረዋል።

በዚህም ስራው በተደራጀ አግባብ እንዲመራ መደረጉን ገልጸው፤ አበረታች ጅምሮች መኖራቸውን አብራርተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.