በክልሉ ከ72 ሚሊየን በላይ ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፣ የካቲት 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመጪው ክረምት ከ72 ሚሊየን በላይ ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሃሰን ገለጹ።
አቶ አሻድሊ ሃሰን በአቡራሞ ወረዳ እየፈሉ ያሉ ችግኞችን እንዲሁም የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች ያሉበትን ሒደት ተመልክተዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በጉብኝቱ ወቅት እንደገለጹት÷ባለፉት ዓመታት የተተገበረው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ተጠባቂ ውጤቶች የተመዘገቡበት ነው፡፡
መርሐ ግብሩ የአካባቢ ሥነ-ምህዳር እንዲያገግም ካበረከተው አስተዋፅኦ ባሻገር በየአካባቢው ማህበረሰቡ ዘርፈ ብዙ ጥቅም እያገኘበት መሆኑን አስገንዝበዋል።
በክልሉ በመጪው ክረምት በሚከናወነው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከ72 ሚሊየን በላይ የተለያዩ ዝርያ ያላቸው ችግኞች እየፈሉ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
ለስኬታማነቱ የሚያግዙ ተግባራት በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች በመተግበር ላይ እንደሆኑ መናገራቸውንም የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡