በመዲናዋ መሬትን በመውረር የተከናወነ ግንባታ ላይ ርምጃ ተወሰደ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) መሬት ባንክ የገባ መሬትን በመውረር በተከናወነ ግንባታ ላይ ርምጃ መውሰዱን የአዲስ አበባ ከተማ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን አስታወቀ፡፡
በአቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ ወረዳ 2 መሬት ባንክ የገባን 1ሺህ ካ.ሜ መሬት ሁለት ግለሰቦች በሕገወጥ መንገድ የ2012 ዓ.ም ካርታ አለን በሚል የግንባታ ፍቃድ በማውጣትና ቦታውን በማጠር ግንባታ ለማከናወን ሲሞክሩ መያዛቸው ተገልጿል፡፡
የተከናወነውን ሕገ-ወጥ ግንባታ ማፍረሱን የገለጸው ባለስልጣኑ÷ጥፋተኞችን በሊዝ አዋጁ ተጠያቂ ለማድረግ በሒደት ላይ መሆኑን ጠቁሟል፡፡
በሕገ-ወጦች ላይ የሚወስደው ርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ማስገንዘቡን የባለስልጣኑ መረጃ ያመላክታል፡፡
የከተማዋ ነዋሪዎች ደንብ የሚተላለፉ ግለሠቦችን በ9995 ነፃ የስልክ መስመር በመደወል ጥቆማ እንዲሰጡም ጥሪ አቅርቧል።