ወንድማማችነትና ሕብረ ብሄራዊ አንድነትን ይበልጥ ለማጠናከር ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ ይገባል- አቶ ሙስጠፌ መሃመድ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ወንድማማችነትና ሕብረ ብሄራዊ አንድነትን ይበልጥ ለማጠናከር ሁሉም የበኩሉን ሚና ሊወጣ ይገባል ሲሉ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሃመድ ገለጹ፡፡
የአፋር እና ሶማሌ ወንድም ሕዝብ ታላቅ የጋራ የኢፍጣር መርሐ ግብር ዛሬ ምሽት በጅግጅጋ ከተማ ተካሂዷል፡፡
አቶ ሙስጠፌ መሃመድ በዚህ ወቅት ÷ በኢፍጣር መርሐ ግብሩ ለታደሙ እንግዶች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በመልዕክታቸውም ኢትዮጵያ ከለውጡ ወዲህ በተለያዩ ዘርፎች በርካታ ስኬቶችን ማስመዝገብ እንደቻለች አስረድተዋል፡፡
ለአብነትም ከለውጡ በፊት አጋር ተብለው የነበሩ ክልሎች አሁን በፖለቲካው ዋና ተሳታፊ መሆን መቻላቸውን ነው የገለጹት፡፡
በወንድማማች የአፋርና ሶማሌ ሕዝብ መካከል አለመግባባቶች ተፈጥረው እንደነበር አስታውሰው ÷ ችግሩን ለመፍታት የፌዴራል መንግስት ከሁለቱ ክልሎች ጋር ሰፊ ጥረት ማድረጉንና በዚህም ውጤት መገኘቱን አውስተዋል፡፡
በቀጣይም የአፋርና ሶማሌ ክልሎችን የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር፣ የልማት ተጠቃሚነት እና አብሮነት ለማጠናከር በትኩረት ይሰራል ነው ያሉት፡፡
ወንድማማችነትና ሕብረ ብሄራዊ አንድነትን ይበልጥ ለማጠናከርም ሁሉም ዜጋ የበኩሉን ሚና ሊወጣ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በታሪኩ ለገሰ