ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር ) በመሬት መንሸራተት አደጋ የተፈናቀሉ ወገኖችን የማቋቋም ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳሰቡ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ አጋጥሞ በነበረው የመሬት መንሸራተት አደጋ የተፈናቀሉ ወገኖችን በዘላቂነት ለማቋቋም የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።
ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) በወረዳው ቡርዳ ንዑስ መንደር ተገኝተው በአደጋው የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም እየተሰሩ ያሉ ተግባራትን ጎብኝተዋል።
በጉብኝታቸው ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለማቋቋም የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ መሆናቸውን መመልከታቸውን ገልጸው፤ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።
የመንገድ፣ የመብራትና ሌሎች የመሠረተ ልማት ጥያቄዎችን ለመፍታት ከሚመለከተው ክፍል ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ መግለጻቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ አመላክቷል፡፡
በአደጋው ጉዳት ለደረሰባቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚደረጉ ማህበራዊና ስነ-ልቦናዊ ድጋፎች ተጠናክረው መቀጠል እንደሚገባቸው አመላክተዋል።