የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መሥተዳድር ምክር ቤት የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳለፈ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መሥተዳድር ምክር ቤት ባካሄደው 20ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ አጀንዳዎቸ ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን አሳልፏል።
የኢንቨስትመንት አሥተዳደርን ለማስፈፀም በወጣ ደንብ፣ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታ ሲለቀቅ የሚከፈል ካሳ እና መልሶ ማቋቋምን በተመለከተ በወጣ መመሪያ እንዲሁም በክልሉ ማዕከላት የሚገነቡ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሕንጻ ግንባታን በተመለከተ የቀረበ የውሳኔ ሐሳብ ላይ ተወያይቷል፡፡
በቀረቡ ረቂቅ ደንቦችና መመሪያዎች ላይ ተወያይቶ በየዘርፉ የሚሠሩ ሥራዎችን በሕግ ማዕቀፍ በመምራትና በአሠራር በመደገፍ ለተሻለ ውጤት ለማብቃት የሚያስችሉ መሆኑን በማመን ከነማሻሻያቸው አፅድቋል፡፡
በክልሉ ማዕከላት የሚገነቡ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሕንጻ ግንባታ በተመለከተ በቀረበ የውሳኔ ሐሳብ ላይ በመወያየት አቅጣጫ ማስቀመጡን የርዕሰ መሥተዳድር ጽሕፈት ቤት መረጃ አመላክቷል፡፡
እንዲሁም በክልሉ የማዕድን ልማት ዘርፍ ያሉ አበረታች ሥራዎችን አጠናክሮ የግሉን ዘርፍ በስፋት በማሳተፍና ክልሉ ባለው እምቅ ዐቅም ልክ በማልማት የዘርፉን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚያስችሉ ቀጣይ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል፡፡