ጃይካ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን የልማት ትብብር አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 10፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴዔታ አምባሳደር ምሥጋኑ አርጋ የጃፓን ዓለም አቀፍ የትብብር ኤጀንሲ (ጃይካ) ምክትል ፕሬዚዳንት ከሆኑት አንዶ ናኦኪን ጋር ተወያይተዋል፡፡
በዚሁ ወቅት ጃይካ ለኢትዮጵያ የልማት ሥራ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ማበርከቱን ያነሱት አምባሳደር ምሥጋኑ፤ በተለይም በዐቅም ግንባታ፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር እና በካይዘን ፍልስፍና ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡
በተጨማሪም በጤና፣ ግብርና እና አምራች ዘርፎች የሚያደርገውን ድጋፍ ጠቅሰው፤ ምክትል ፕሬዚዳንቱ በኢትዮጵያ ያደረጉት ጉብኝትም የልማት ትብብሩን የበለጠ ያግዛል ብለዋል፡፡
የጃፓን ኩባንያዎች በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች የተፈጠሩ የንግድና የኢንቨስትመንት ዕድሎችን እንዲጠቀሙ ጥሪ ማቅረባቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡
አንዶ ናኦኪን በበኩላቸው ኢትዮጵያ ያደረገችውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ አድንቀው፤ ተቋማቸው ከኢትዮጵያ ጋር በተለያዩ ዘርፎች የሚያደርገውን የልማት ትብብር አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡