Fana: At a Speed of Life!

በውጭ ሀገር የተሰጠን ፍርድ በማስፈጸም 2 ነጥብ 25 ሚሊየን ዩሮ ገቢ ተገኘ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 10፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በኔዘርላንድስ የሄግ ቋሚ የግልግል ዳኝነት ፍርድ ቤት ከ300 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ ካሳ እንድትከፍል በቀረበባት ዓለም ዓቀፍ የኢንቨስትመንት ግልግል ዳኝነት ክስ ላይ ክርክር ተደርጎ ማስፈጸም መቻሉን የፍትሕ ሚኒስትር ወ/ሮ ሐና አርዓያሥላሴ ገለጹ፡፡

ከክርክሩ ጀምሮ የፍርድ ውሳኔውን እስከ ማስፈጸም ድረስ በፍትሕ ሚኒስቴር አስተባባሪነት ከማዕድን ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀት 2 ነጥብ 25 ሚሊየን ዩሮ ለኢትዮጵያ ገቢ ማድረግ መቻሉ ተገልጿል፡፡

የግልግል ዳኝነት ፍርዱን በውጭ ሀገር ማስፈጸም መቻሉ ብዙ አንድምታዎች ያሉት መሆኑን ሚኒስትሯ አብራርተዋል።

ውጤቱ ኢትዮጵያ በሁለትዮሽ የኢንቨስትመንት ስምምነቶች የገባችውን ቃል አክብራ በየትኛውም ፍርድ አደባባይ ቀርባ መብትና ጥቅሞቿን እንደምታስከብር ማሳያ ነው ብለዋል።

በተጨማሪም የፍርዱ መፈጸም በኢትዮጵያ ላይ ያለአግባብ የሚቀርቡ ክሶችን መርታት ብቻ ሳይሆን ለክርክሩ የሚወጣው ወጪ ጭምር የሚሰላበት መሆኑን አመልክተዋል።

ይህም ኢንቨስትመንትን መሠረት የሚያደርጉ አግባብነት የሌላቸውን ክሶች የመከላከል ውጤት እንደሚኖረው መግለጻቸውን ሚኒስቴሩ ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን የላከው መረጃ ጠቁሟል።

ፍርዱን ከሀገር ውጪ ተከታትሎ ማስፈጸም መቻሉ በመሰል ዓለም ዓቀፍ ጉዳዮች ሀገራዊ መብት እና ጥቅምን በማስከበር ረገድ እየተፈጠረ ላለው የማስፈጸም አቅም እና የተቋማት ቅንጅት ማሳያ እንደሆነም ወ/ሮ ሐና አስረድተዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.