ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ከ3 ሚሊየን በላይ የስራ ዕድሎችን መፈጠራቸውን ገለጹ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ባለፉት 8 ወራት ከ3 ሚሊየን በላይ የስራ ዕድሎችን መፍጠር መቻሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለፁ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ፤ ባለፉት 8 ወራት በተመዘገበ መረጃ በሀገር ውስጥ 2 ነጥብ 8 ሚሊየን ዜጎች የስራ ዕድል ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ከ300 ሺህ በላይ የሚሆኑ ዜጎች ደግሞ በውጭ ሀገራት የስራ ስምሪት ዕድል ማግኘታቸውን ገልጸው፤ ከ45 ሺህ በላይ ዜጎች በሪሞት ጆብ ወይም በዲጂታል መንገድ ስራ ማግኘት መቻላቸውን ገልጸዋል፡፡
የግብርናው ዘርፍ 40 በመቶ፣ ኢንዱስትሪ 20 በመቶ፣ ሰርቪስ 38 በመቶ የስራ ዕድሎች የተገኙባቸው ዘርፎች መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ከሴክተሮች በተጨማሪ በኮሪደር ስራዎች እና ልዩ ልዩ ኢኒሼቲቮች በርካታ የስራ ዕድሎችን ፈጥረናል ብለዋል፡፡
ካለው አምራች ሀይል አንፃር አሁን ያለው የስራ ዕድል በቂ አለመሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በቀጣይም ያለውን የስራ ፍላጎት በሚመጥን መልኩ ዜጎችን የስራ ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሰራ አመላክተዋል፡፡