በክልሉ 250 ሺህ ወጣቶችን የውጭ ሀገራት የሥራ ስምሪት ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 12፣2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሚቀጥለው ዓመት 250 ሺህ ወጣቶችን የውጭ ሀገራት የሥራ ስምሪት ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው ገለፁ፡፡
በቡታጅራ ክላስተር የሚገኙ የልዩ ልዩ ሴክተር መስሪያ ቤቶች አፈጻጸም ግምገማ እየተካሄደ ነው፡፡
በመድረኩ በክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን፣ በንግድና ገበያ ልማት፣ በኢንቨስትመንት እና ኢንዱስትሪ ልማት ሴክተር መስሪያ ቤቶች የተከናወኑ ተግባራት ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
በዚህ ወቅት ርዕስ መስተዳድሩ እንደገለጹት ÷ በኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ለወሰዱ ወጣቶች ተጨማሪ የአቅም ግንባታ ስልጠና በመስጠት ዲጂታል መንገድን በመጠቀም ብቻ ባሉበት ሆነው ስራ መስራት የሚችሉበትን ስርዓት ለመዘርጋት እየተሰራ ነው።
ሁሉም ሴክተሮች የሥራ እድል ፈጠራ እና የኑሮ ውድነትን ማረጋጋት የሚያስችል ስርዓት መፍጠር እንዳለባቸው መናገራቸውንም የክልሉ ኮሙዩኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
በክላስተር ደረጃ ቅንጅታዊ አሰራርን በመተግበር የላቀ ውጤት እንዲመዘገብ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡