በሶማሌ ክልል 20 ሚሊየን ኩንታል ምርት መሰብሰቡ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሶማሌ ክልል በተለያየ ሰብል ከለማ 730 ሺህ ሔክታር 20 ሚሊየን ኩንታል ምርት መገኘቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አሕመድ ኑር አስታወቁ፡፡
1 ሚሊየን 31 ሺህ ሔክታር በዘር ለመሸፈን ታቅዶ 970 ሺህ ሔክታር ማልማት መቻሉን ጠቅሰው፤ ከዚህ ውስጥ እስከ አሁን በ730 ሺህ ሔክታር ላይ የለማው ሰብል ተሰብስቦ 20 ሚሊየን ኩንታል ምርት ተገኝቷል ብለዋል፡፡
ከተሰበሰቡት የምርት ዓይነቶች መካከልም፤ በቆሎ፣ ሽንኩርት፣ ሙዝ እና ሌሎችም እንደሚገኙበት አብራርተዋል፡፡
በሌሎች ሰብሎችም የተገኘው ምርት አበረታች መሆኑን በመግለጽ፤ በቀጣይ ከዚህ በተሻለ ለማግኘት እየተሠራ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡
ከለውጡ በፊት በክልሉ ሲታረስ የነበረው ከ400 ሺህ ሔክታር አለመብለጡን እና በአሁኑ ወቅት ግን 970 ሺህ ሔክታር መሬት ማረስ መቻሉን አስረድተዋል፡፡
በ2018 ዓ.ም የሚታረሰውን መሬት ከ1 ሚሊየን ሔክታር በላይ ለማድረስ ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው ያሉት ምክትል ኃላፊው፤ ለአብነትም በበቆሎ፣ በስንዴ፣ በሽንኩርት እንዲሁም በፍራፍሬ ዘርፎች በተሠሩ ሥራዎች ጥሩ ውጤት ተገኝቷል ብለዋል፡፡
በክልሉ ያሉትን የተፈጥሮ ሀብቶች በመጠቀም ምርታማነትን ለመጨመር በልዩ ትኩረት እንደሚሠራም ገልጸዋል፡፡
በታሪኩ ለገሰ