Fana: At a Speed of Life!

ከስቅለቱ የምንማረው ይቅርታ ማድረግን፣ ትህትናንና መከባበርን ነው – ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌል

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 10፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ከኢየሱስ ክርስቶስ ስቅለት የምንማረው የሰው ልጆች እርስ በርሳቸው ይቅርታ ማድረግን፣ ትህትናን እና መከባበርን ነው ሲሉ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌል ገለጹ።

የኢየሱስ ክርስቶስ የስቅለት በዓል በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን እምነት ተከታዮች በስግደት፣ በፆምና በጸሎት እየተከበረ ነው።

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሊቀጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌል በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፥ ከስቅለት በዓል የምንማረው የሰው ልጆች እርስ በርሳቸው ይቅርታ ማድረግን፣ ትህትናን እና መከባበርን ነው።

ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን ለማዳንና ሃጥያታቸውን ለማንጻት መስቀል ተሸክሞ መሰቃየቱን፣ መገረፉን፣ በችንካር መቸንከሩንና መሰቀሉን በማውሳት በሕማማተ መስቀል ፍጹም ፍቅርንና ይቅርታን ማስተማሩን ገልጸዋል።

የሰው ልጆች ይቅር መባባል፣ እርስ በርሳቸው መዋደድ እና መከባበር አለባቸው ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌል÷ “ፈጣሪ እኛን ይቅር ብሎናል እኛም የበደሉንን ይቅር በማለት በፍቅርና በአብሮነት መኖርን ማጠናከር አለብን” ሲሉ ተናግረዋል።

መጪውን የትንሳዔ በዓልንም አቅም የሌላቸውን ወገኖች በመደገፍ ማክበር እንደሚገባ አባታዊ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.